[1] የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደ ሰጠን እዩ፥ እንዲሁም ነን፤ ስለዚህም ዓለም እርሱን ስላላወቀው እኛንም አያውቀንም።
[2] ወንድሞቻችን ሆይ፥ ዛሬስ የእግዚአብሔር ልጆች ነን፤ ምን እንደምንሆንም ገና አልታወቀልንም፤ በሚታወቅልን ጊዜ ግን እንደ እርሱ እንደምንሆን እናውቃለን እርሱ እንደ ሆነ እርሱን እናየዋለንና።
[3] በእርሱም የሚታመን ሁሉ እርሱ ንጹሕ እንደ ሆነ ራሱን ያነጻል።
[4] ኀጢአትን የሚሠራት ሁሉ እርሱ በደልን ደግሞ ያደርጋል፤ ኀጢአት በደል ናትና።
[5] እርሱም ኀጢአትን ያስወግድ ዘንድ እንደ ተገለጠ ታውቃላችሁ፤ በእርሱም ኀጢአት የለም።
[6] በእርሱም የሚኖር ሁሉ አይበድልም፤ የሚበድልም ሰው አያየውም፥ አያውቀውምና።
[7] ልጆቼ ሆይ፥ ማንም አያስታችሁ እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ጻድቅ ነው፤
[8] ኀጢአትን የሚሠራትም ከሰይጣን ወገን ነው፤ ጥንቱን ሰይጣን በድሎአልና፤ ስለዚህ የሰይጣንን ሥራ ይሽር ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ።
[9] ከእግዚአብሔር የሚወለድ ሁሉ ኀጢትን አይሠራም፤ ዘሩ በእርሱ ይኖራልና፤ ኀጢአትንም ሊሠራ አይችልም፤ ከእግዚአብሔር ተወልዶአልና።
[10] በዚህም የእግዚአብሔር ልጆችና የሰይጣን ልጆች ይታወቃሉ፤ ጽድቅንም የማይሠራ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተወለደ አይደለም፤ ወንድሙንም የማይወድ እንዲሁ ነው።
[11] እርስ በርሳችን እንዋደድ የምትል ከመጀመሪያ የሰማችኋት መልእክት ይህች ናት።
[12] ከክፉ ወገን እንደ ሆነ፥ ወንድሙንም እንደ ገደለው እንደ ቃየል አይደለም፤ ስለምንስ ገደለው? የእርሱ ሥራ ክፉ፥ የወንድሙ ግን ጽድቅ ስለ ነበር ነው።
[13] ወንድሞቻችን ሆይ፥ ምንም ዓለም ቢጠላችሁ አታድንቁ።
[14] እኛ ግን፥ ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ባልንጀራችንን እንወዳለንና፤ ባልንጀራውን የማይወድ ግን በጨለማ ይኖራል።
[15] ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳይ የሆነም ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት በእርሱ እንደማይኖር ታውቃላችሁ።
[16] በዚህም ፍቅርን ዐወቅነው፤ እርሱ ራሱን ስለ እኛ አሳልፎ ሰጥቶአልና፤ እኛም ስለ ባልንጀሮቻችን ራሳችንን አሳልፈን ልንሰጥ ይገባናል።
[17] የዚህ ዓለም ንብረት ያለው ወንድሙንም ተቸግሮ አይቶ ምጿትን የሚከለክለው የእግዚአብሔር ፍቅር እንዴት በእርሱ ላይ ይኖራል?
[18] ልጆቼ ሆይ፥ በምግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንፋቀር።
[19] ልባችንም በእኛ ላይ በሚፈርድበት ሁሉ ከእውነት እንደ ሆነ በእዚህ እናውቀዋለን።
[20] ልባችንንም በፊቱ እናሳርፋለን፤ እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉንም ያውቃል።
[21] ወንድሞቻችን ሆይ፥ ልባችን የማይወቅሰን ከሆነ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ መወደድ አለን።
[22] የምንለምነውንም ከእርሱ እናገኛለን፤ ትእዛዙን እንጠብቃለንና፤ በፊቱም ደስ የሚያሰኘውን እንሠራለንና።
[23] ትእዛዙም ይህቺ ናት፤ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናምን ዘንድ፥ ትእዛዙንም እንደ ሰጠን እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ።
[24] ትእዛዙን የሚጠብቅም በእርሱ ይኖራል፤ እርሱም በእርሱ ያድራል፤ በዚህም ከእኛ ጋር እንደሚኖር ከሰጠን ከመንፈሱ እናውቃለን።