[1] ወንድሞቻችን ሆይ፥ መንፈስን ሁሉ አትመኑ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኟች ነቢያት ወደ ዓለም መጥተዋልና።
[2] የእግዚአብሔርን መንፈስና የሐሰትን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የሚያምን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው።
[3] ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማያምን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም እንደሚመጣ የሰማችሁት ሐሳዊ መሲሕ ነው፤ አሁንም እንኳ በዓለም ውስጥ አለ።
[4] ልጆች ሆይ፥ እናንተ ግን ከእግዚአብሔር ናችሁ፤ ክፉውንም አሸንፋችሁታል፤ በዓለም ውስጥ ካለው ይልቅ ከእናንተ ጋር ያለው ይበልጣልና።
[5] እነርሱ ግን ከዓለም ናቸው፤ ስለዚህም ከዓለም የሆነውን ይናገራሉ፤ ዓለምም ይሰማቸዋል።
[6] እኛስ ከእግዚአብሔር ነን፤ እግዚአብሔርን የሚያውቀውም ይሰማናል፤ ከእግዚአብሔር ያልሆነ ግን አይሰማንም፤ በዚህም የእውነትን መንፈስና የሐሰትን መንፈስ እናውቃለን።
[7] ወንድምቻችን ሆይ፥ እርስ በርሳችን እንፋቀር፤ ፍቅር ከእግዚአብሔር ነውና፤ የሚፋቀርም ሁሉ እርሱ ከእግዚአብሔር ተወለደ፤ እግዚአብሔርንም ያውቀዋል።
[8] ወንድሙን የማያፈቅር እግዚአብሔርን አያውቅም፤ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና።
[9] በዚህም የእግዚአብሔር ፍቅሩ በእኛ ላይ ታወቀ፤ በእርሱ በሕይወት እንኖር ዘንድ አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና።
[10] የእግዚአብሔርም ፍቅሩ ይህ ነው፤ እርሱ ወደደን እንጂ የወደድነው እኛ አይደለንም፤ ኀጢአታችንንም ያስተሰርይልን ዘንድ ልጁን ላከው።
[11] ወንድሞቻችን ሆይ፥ እግዚአብሔር ይህን ያህል ከወደደን፥ እኛም እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል።
[12] እግዚአብሔርንስ ከቶ ያየው ሰው የለም፤ እርስ በርሳችን ከተዋደድን ግን እግዚአብሔር አድሮብን ይኖራል፤ ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ይሆናል።
[13] ከመንፈሱ ስለ ሰጠን በእርሱ እንደምንኖር እርሱም በእኛ አድሮ እንደሚኖር በዚህ እናውቃለን።
[14] እኛም አይተናል፤ አብም ልጁን የዓለም መድኀኒት ሊሆን እንደ ላከው እንመሰክራለን።
[15] ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ የሚያምን ሁሉ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ይኖራል፤ እርሱም ከእግዚአብሔር ጋር ይኖራል።
[16] እኛስ የእግዚአብሔር ፍቅር ከእኛ ጋር እንዳለ ዐውቀን አምነናል፤ እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ በፍቅር የሚኖርም ከእግዚአብሔር ጋር ይኖራል፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ይኖራል።
[17] በዚህም በፍርድ ቀን በእርሱ ዘንድ መወደድን እናገኝ ዘንድ ከእኛ ጋር ያለችው የእግዚአብሔር ፍቅር ትፈጸማለች፤ እርሱ እንዳለ እኛ ደግሞ እንዲሁ በዚህ ዓለም ነንና።
[18] በፍቅር መፈራራት የለም፤ ፍጽምት ፍቅር ፍርሀትን ወደ ውጭ ታወጣታለች እንጂ፤ ፍርሀት ቅጣት አለባት፤ የሚፈራም በፍቅር ፍጹም አይደለም።
[19] እኛም እርስ በርሳችን እንዋደድ፤ እግዚአብሔርንም እንውደደው፤ እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና።
[20] እግዚአብሔርን እወደዋለሁ የሚል፥ ወንድሙን ግን የሚጠላ ሐሰተኛ ነው፤ የሚያየውን ወንድሙን የማይወድ ግን የማያየውን እግዚአብሔርን እንደምን ሊወድደው ይችላል?።
[21] እግዚአብሔርን እንወድደው ዘንድ፥ ወንድማችንንም እንወድ ዘንድ ከእርሱ የተቀበልነው ትእዛዝ ይህ ነው ፥ እግዚአብሔርን የሚወድ ሁሉ ወንድሙን ይወድዳል።