[1] ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና በጆሮአችን የሰማነውን፥ በዐይኖቻችንም ያየነውን፥ የተመለከትነውንም፥ እጆቻችንም የዳሰሱትን እንነግራችኋለን።
[2] ሕይወት ለእኛ ተገልጻለችና አየናት፤ ምስክርም ሆንን፤ ለእናንተም ከአብ ዘንድ ያለችውንና ለእኛ የተገለጠችውን የዘለዓለምን ሕይወት እንነግራችኋለን።
[3] እናንተም ከእኛ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ ያየናትንና የሰማናትን እንነግራችኋለን፤ አንድነታችንም ከአብና ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው።
[4] ደስታችሁም ፍጽምት ትሆን ዘንድ ይህን እንጽፍላችኋለን።
[5] ከእርሱም የሰማናት፥ ለእናንተም የምንነግራችሁ መልእክት ፥ “እግዚአብሔር ብርሃን ነው፤ ጨለማም በእርሱ ዘንድ ጥቂትስ እንኳ የለም ” የምትል ይህች ናት።
[6] ከእርሱም ጋር አንድነት አለን ብንላችሁ፥ በጨለማም ብንመላለስ ሐሰት እንናገራለን፤ እውነትንና ቅንነትንም አናደርግም።
[7] እርሱ ብርሃን እንደ ሆነ በብርሃን ብንመላለስ ግን እኛ እርስ በርሳችን አንድነት አለን፤ የኢየሱስ ክርስቶስም ደም ከኀጢአታችን ሁሉ ያነጻናል።
[8] ኀጢአት የለብንም ብንል ግን ራሳችንን እናስታለን፤ የቀና ነገርም በእኛ ዘንድ የለም።
[9] ኀጢአታችንን አምነን ብንናገር ግን ኀጢአታችንን ይቅር ይለን ዘንድ የታመነ ነው፤ ቸርም ነው፤ ከበደላችንም ሁሉ ያነጻናል።
[10] አልበደልንም ብንል ግን እርሱን ሐሰተኛ እናደርገዋለን፤ ቃሉም በእኛ ዘንድ የለም።