[1] ልጆቼ ሆይ፥ እንዳትበድሉ ይህን እጽፍላችኋለሁ፤ የሚበድልም ቢኖር ከአብ ዘንድ ጰራቅሊጦስ አለን፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ኀጢአታችንን ያስተሰርይልን ዘንድ ጻድቅ ነው።
[2] ስለ እኛ ብቻ አይደለም፤ ስለ ዓለምም ሁሉ እንጂ።
[3] ትእዛዙንም ብንጠብቅ በዚህ እንደ ዐወቅነው እናውቃለን።
[4] ዐውቀዋለሁ የሚል ትእዛዙንም የማይጠብቅ ሐሰተኛ ነው፤ የእግዚአብሔር እውነትም በእርሱ ዘንድ የለም።
[5] ቃሉን የሚጠብቅ ግን በእውነት የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ ላይ ተፈጽሟል፤ በዚህም በእርሱ እንዳለን እናውቃለን።
[6] በእርሱ እኖራለሁ የሚል እርሱ እንደ ተመላለሰ ራሱ ደግሞ ሊመላለስ ይገባዋል።
[7] ወንድሞቻችን ሆይ፥ አዲስ ትእዛዝ የምጽፍላችሁ አይደለም፤ ቀድሞ በእናንተ ዘንድ የነበረችውን ነባር ትእዛዝ ነው እንጂ፤ ይህ የሰማችሁት ቃል ነባር ትእዛዝ ነውና።
[8] ዳግመኛም አዲስ ትእዛዝ እጽፍላችኋለሁ፤ ይህም በእርሱ በእናንተም እውነተኛ ነው፤ ጨለማ አልፋለችና፤ እውነተኛ ብርሃንም ፈጽሞ ታይቶአልና።
[9] በብርሃን ውስጥ አለሁ የሚል ወንድሙን የሚጠላ ገና እስካሁን በጨለማ ውስጥ አለ።
[10] ወንድሙን የሚወድ ግን በብርሃን ይኖራል፤ በእርሱ ዘንድም መሰናክል የለበትም።
[11] ወንድሙን የሚጠላ ግን እርሱ በጨለማ አለ፤ በጨለማም ይመላለሳል፤ የሚሄድበትንም አያውቅም፤ ጨለማው ዐይኑን አሳውሮታልና።
[12] ልጆቼ ሆይ፥ በስሙ ኀጢአታችሁ ተሰርዮላችኋልና እጽፍላችኋለሁ።
[13] አባቶች ሆይ፥ በመጀመሪያ የነበረውን ዐውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ፤ ጐልማሶች ሆይ፤ ክፉውን ድል ነሥታችሁታልና እጽፍላችኋለሁ፤ ልጆቼ ሆይ፤ አብን ዐውቃችሁታልና እጽፍላችኋለሁ።
[14] አባቶች ሆይ፥ በመጀመሪያ የነበረውን ዐውቃችሁታልና እጽፍላችኋለሁ። ጐልማሶች ሆይ፥ ብርቱዎች ናችሁና፥ የእግዚአብሔር ቃልም በእናንተ ዘንድ ጸንቶ ይኖራልና፥ ክፉውንም ድል ነሥታችሁታልና እጽፍላችኋለሁ።
[15] ዓለሙንና በዓለም ያለውን አትውደዱ፤ ዓለሙን የሚወድ ግን የአብ ፍቅር በእርሱ የለም።
[16] በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኟትና የዐይን አምሮት፥ ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም እንጂ ከአብ አይደለም።
[17] ዓለሙ ያልፋል፤ ምኟቱም ያልፋል፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሰው ግን ለዘለዓለም ይኖራል።
[18] ልጆቼ ሆይ፥ ይህቺ ሰዓት መጨረሻዋ ሰዓት ናት፤ ሐሳዊ መሲሕ እንደሚመጣ እንደ ሰማችሁ ዛሬም ብዙዎች ሐሰተኟች መሲሖች ተነሥተዋል፤ ስለዚህም መጨረሻዋ ሰዓት እንደ ሆነች እናውቃለን።
[19] ከእኛ ወገን ያልሆኑ ከእኛ ወጥተዋል፥ ከእኛ ወገንስ ቢሆኑ ኖሮ አብረውን በኖሩ ነበር፤ ነገር ግን ሁሉም ከእኛ ወገን እንዳልሆኑ ይገለጡ ዘንድ ተለዩ።
[20] እናንተስ ከቅዱሱ ያገኛችሁት ቅብዐት አላችሁ፤ ሁሉንም ታውቃላችሁ።
[21] እውነትን የምታውቁ ስለሆናችሁ፥ ውሸትም ሁሉ ከእውነት እንዳልሆነ ስለምታውቁ እንጂ እውነትን እንደማታውቁ አድርጌ አልጽፍላችሁም።
[22] ኢየሱስ መሲሕ አይደለም ብሎ ከሚክድ በቀር ሐሰተኛ ማን ነው? አብንና ወልድን የሚክድ ሐሳዊ መሲሕ ይህ ነው።
[23] ወልድን የሚክድ ሁሉ አብ እንኳ የለውም፤ በወልድ የሚያምን ግን አብ አለው፤
[24] እናንተስ ቀድሞ የሰማችሁት ትምህርት በእናንተ ዘንድ ጸንቶ ይኑር፤ ቀድሞ የሰማችሁትም ትምህርት በእናንተ ዘንድ ካለ እናንተም በአብና በወልድ ትኖራላችሁ።
[25] እርሱም የሰጠን ይህች ተስፋ ለዘለዓለም ሕይወት ናት።
[26] ስለሚያስቱአችሁም ይህን ጽፌላችኋለሁ።
[27] እናንተ ግን ከእርሱ የተቀበላችኋት ቅብዐት አለቻችሁ፤ በእናንተ ዘንድም ትኖራለች፤ ማንም ሊያስተምራችሁ አትሹም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር መንፈስ ሁሉን ያስተምራችኋል፤ የታመነም ነው፤ ሐሰትም አይደለም እንደ ተማራችሁትም በእርሱ ኑሩ።
[28] አሁንም ልጆቼ ሆይ፥ በሚገለጥበት ጊዜ መወደድን እናገኝ ዘንድ፥ በሚመጣበትም ጊዜ ከእርሱ የተነሣ እንዳናፍር በእርሱ ጸንታችሁ ኑሩ።
[29] እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ ብታውቁ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ከእርሱ እንደ ተወለደ ዕወቁ።