[1] በዚህም ወራት ደቀ መዛሙርት እየበዙ ሲሄዱ ከግሪክ አገር መጥተው የነበሩት አይሁድ በይሁዳ ኖረው በነበሩት አይሁድ አንጐራጐሩባቸው፥ በየቀኑ በተሠራው አገልግሎት መበለቶቻቸውን ችላ ይሉባቸው ነበርና።
[2] አሥራ ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሁሉን ጠርተው እንዲህ አሉአቸው። የእግዚአብሔር ቃል ትተን ማዕድን እናገለግል ዘንድ የሚገባ ነገር አይደለም።
[3] ወንድሞች ሆይ፥ በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብም የሞላባቸውን ሰባት ሰዎች ከእናንተ ምረጡ፥ ለዚህም ጉዳይ እንሾማቸዋለን፤
[4] እኛ ግን ለጸሎትና ቃሉን ለማገልገል እንተጋለን።
[5] ይህም ቃል ሕዝብን ሁሉ ደስ አሰኛቸው፤ እምነትና መንፈስ ቅዱስም የሞላበትን ሰው እስጢፋኖስን ፊልጶስንም ጵሮኮሮስንም ኒቃሮናንም ጢሞናንም ጳርሜናንም ወደ ይሁዲነት ገብቶ የነበረውን የአንጾኪያውን ኒቆላዎስንም መረጡ።
[6] በሐዋርያትም ፊት አቆሙአቸው፥ ከጸለዩም በኋላ እጃቸውን ጫኑባቸው።
[7] የእግዚአብሔርም ቃል እየሰፋ ሄደ፥ በኢየሩሳሌምም የደቀ መዛሙርት ቍጥር እጅግ እየበዛ ሄደ፤ ከካህናትም ብዙ ሰዎች ለሃይማኖት የታዘዙ ሆኑ።
[8] እስጢፋኖስም ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር።
[9] የነፃ ወጪዎች ከተባለችው ምኵራብም ከቀሬናና ከእስክንድርያም ሰዎች ከኪልቅያና ከእስያም ከነበሩት አንዳንዶቹ ተነሥተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር፤
[10] ይናገርበት የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ አልቻሉም።
[11] በዚያን ጊዜ። በሙሴ ላይ በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ነገር ሲናገር ሰምተነዋል የሚሉ ሰዎችን አስነሡ።
[12] ሕዝቡንና ሽማግሌዎችንም ጻፎችንም አናደዱ፥ ቀርበውም ያዙት ወደ ሸንጎም አመጡትና።
[13] ይህ ሰው በዚህ በተቀደሰው ስፍራ በሕግም ላይ የስድብን ነገር ለመናገር አይተውም፤
[14] ይህ የናዝሬቱ ኢየሱስ ይህን ስፍራ ያፈርሰዋል ሙሴም ያስተላለፈልንን ሥርዓት ይለውጣል ሲል ሰምተነዋልና የሚሉ የሐሰት ምስክሮችን አቆሙ።
[15] በሸንጎም የተቀመጡት ሁሉ ትኵር ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን አዩት።