[1] ለሕዝቡም ሲናገሩ የካህናት አለቆችና የመቅደስ አዛዥ ሰዱቃውያንም፥
[2] ሕዝቡን ስለ አስተማሩና በኢየሱስ የሙታንን ትንሣኤ ስለ ሰበኩ ተቸግረው፥ ወደ እነርሱ ቀረቡ፥
[3] እጃቸውንም ጭነውባቸው አሁን መሽቶ ነበርና እስከ ማግሥቱ ድረስ በወኅኒ አኖሩአቸው።
[4] ነገር ግን ቃሉን ከሰሙት ብዙዎች አመኑ፥ የወንዶችም ቍጥር አምስት ሺህ ያህል ሆነ።
[5] -
[6] በነገውም አለቆቻቸውና ሽማግሌዎች ጻፎችም ሊቀ ካህናቱ ሐናም ቀያፋም ዮሐንስም እስክንድሮስም የሊቀ ካህናቱም ዘመዶች የነበሩት ሁሉ በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ፤
[7] እነርሱንም በመካከል አቁመው። በምን ኃይል ወይስ በማን ስም እናንተ ይህን አደረጋችሁ? ብለው ጠየቁአቸው።
[8] በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መንፈስ ቅዱስንም ተሞልቶ እንዲህ አላቸው። እናንተ የሕዝብ አለቆችና ሽማግሌዎች፥
[9] እኛ ዛሬ ለድውዩ ሰው ስለ ተደረገው መልካም ሥራ ይህ በምን እንደዳነ ብንመረመር፥
[10] እናንተ በሰቀላችሁት እግዚአብሔርም ከሙታን ባስነሣው በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይህ ደኅና ሆኖ በፊታችሁ እንደ ቆመ፥ ለእናንተ ለሁላችሁ ለእስራኤልም ሕዝብ ሁሉ የታወቀ ይሁን።
[11] እናንተ ግንበኞች የናቃችሁት፥ የማዕዘን ራስ የሆነው ይህ ድንጋይ ነው።
[12] መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።
[13] ጴጥሮስና ዮሐንስም በግልጥ እንደ ተናገሩ ባዩ ጊዜ፥ መጽሐፍን የማያውቁና ያልተማሩ ሰዎች እንደ ሆኑ አስተውለው አደነቁ፥ ከኢየሱስም ጋር እንደ ነበሩ አወቁአቸው፤
[14] የተፈወሰውንም ሰው ከእነርሱ ጋር ቆሞ ሲያዩ የሚመልሱትን አጡ።
[15] ከሸንጎም ወደ ውጭ ይወጡ ዘንድ አዝዘው። በእነዚህ ሰዎች ምን እንሥራ?
[16] የታወቀ ምልክት በእነርሱ እጅ እንደ ተደረገ በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ሁሉ ተገልጦአልና፥ እንሸሽገው ዘንድ አንችልም፤
[17] ነገር ግን በሕዝቡ ዘንድ አብዝቶ እንዳይስፋፋ፥ ከእንግዲህ ወዲህ ለማንም ሰው በዚህ ስም እንዳይናገሩ እየዛትን እንዘዛቸው ብለው እርስ በርሳቸው ተማከሩ።
[18] ጠርተውም በኢየሱስ ስም ፈጽመው እንዳይናገሩና እንዳያስተምሩ አዘዙአቸው።
[19] ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን መልሰው። እግዚአብሔርን ከመስማት ይልቅ እናንተን እንሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት የሚገባ እንደ ሆነ ቍረጡ፤
[20] እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም አሉአቸው።
[21] እነርሱም እንደ ምን እንደሚቀጡ ምክንያት ስላላገኙባቸው፥ እንደ ገና ዝተው ከሕዝቡ የተነሣ ፈቱአቸው፤ ሰዎች ሁሉ ስለ ሆነው ነገር እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበርና።
[22] ይህ የመፈወስ ምልክት የተደረገለት ሰው ከአርባ ዓመት ይበልጠው ነበርና።
[23] ተፈትተውም ወደ ወገኖቻቸው መጡና የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች ያሉአቸውን ሁሉ ነገሩአቸው።
[24] እነርሱም በሰሙ ጊዜ በአንድ ልብ ሆነው ወደ እግዚአብሔር ድምፃቸውን ከፍ አደረጉ እንዲህም አሉ። ጌታ ሆይ፥ አንተ ሰማዩንና ምድሩን ባሕሩንም በእነርሱም የሚኖረውን ሁሉ የፈጠርህ፥
[25] በመንፈስ ቅዱስም በብላቴናህ በአባታችን በዳዊት አፍ። አሕዛብ ለምን አጕረመረሙ? ሕዝቡስ ከንቱን ነገር ለምን አሰቡ?
[26] የምድር ነገሥታት ተነሡ አለቆችም በጌታና በተቀባው ላይ አብረው ተከማቹ ብለህ የተናገርህ አምላክ ነህ።
[27] -
[28] በቀባኸው በቅዱሱ ብላቴናህ በኢየሱስ ላይ ሄሮድስና ጴንጤናዊው ጲላጦስ ከአሕዛብና ከእስራኤል ሕዝብ ጋር፥ እጅህና አሳብህ እንዲሆን አስቀድመው የወሰኑትን ሁሉ ሊፈጽሙ፥ በዚች ከተማ በእውነት ተሰበሰቡ።
[29] -
[30] አሁንም፥ ጌታ ሆይ፥ ወደ ዛቻቸው ተመልከት፤ ለመፈወስም እጅህን ስትዘረጋ በቅዱስ ብላቴናህም በኢየሱስ ስም ምልክትና ድንቅ ሲደረግ፥ ባሪያዎችህ በፍጹም ግልጥነት ቃልህን እንዲናገሩ ስጣቸው።
[31] ከጸለዩም በኋላ ተሰብስበው የነበሩበት ስፍራ ተናወጠ፥ በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ የእግዚአብሔርንም ቃል በግልጥ ተናገሩ።
[32] ያመኑትም ሕዝብ አንድ ልብ አንዲትም ነፍስ ነበሩአቸው፥ ገንዘባቸውም ሁሉ በአንድነት ነበረ እንጂ ካለው አንድ ነገር ስንኳ የራሱ እንደ ሆነ ማንም አልተናገረም።
[33] ሐዋርያትም የጌታን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ በታላቅ ኃይል ይመሰክሩ ነበር፤ በሁሉም ላይ ታላቅ ጸጋ ነበረባቸው።
[34] በመካከላቸው አንድ ስንኳ ችግረኛ አልነበረምና፤ መሬት ወይም ቤት ያላቸው ሁሉ እየሸጡ የተሸጠውን ዋጋ ያመጡ ነበርና፥
[35] በሐዋርያትም እግር አጠገብ ያኖሩ ነበር፤ ማናቸውም እንደሚፈልግ መጠን ለእያንዳንዱ ያካፍሉት ነበር።
[36] ትውልዱም የቆጵሮስ ሰው የነበረ አንድ ሌዋዊ ዮሴፍ የሚሉት ነበረ፥ እርሱም በሐዋርያት በርናባስ ተባለ ትርጓሜውም የመጽናናት ልጅ ነው፤
[37] እርሻም ነበረውና ሽጦ ገንዘቡን አምጥቶ ከሐዋርያት እግር አጠገብ አኖረው።