Skip to content
Opens in a new window

[1] በደኅና ከደረስን በኋላ በዚያን ጊዜ ደሴቲቱ መላጥያ እንድትባል አወቅን።

[2] አረማውያንም የሚያስገርም ቸርነት አደረጉልን፤ ዝናብ ስለ ሆነም ስለ ብርዱም እሳት አንድደው ሁላችንን ተቀበሉን።

[3] ጳውሎስ ግን ብዙ ጭራሮ አከማችቶ ወደ እሳት ሲጨምር እፉኝት ከሙቀት የተነሣ ወጥታ እጁን ነደፈችው።

[4] አረማውያንም እባብ በእጁ ተንጠልጥላ ባዩ ጊዜ፥ እርስ በርሳቸው። ይህ ሰው በእርግጥ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ከባሕርም ስንኳ በደኅና ቢወጣ የእግዚአብሔር ፍርድ በሕይወት ይኖር ዘንድ አልተወውም አሉ።

[5] እርሱ ግን እባቢቱን ወደ እሳት አራገፋት አንዳችም አልጐዳችውም፤

[6] እነርሱም። ሊያብጥ ወይም ወዲያው ሞቶ ሊወድቅ ነው ብለው ይጠባበቁት ነበር ብዙ ጊዜ ግን ሲጠባበቁ በእርሱ ላይ የሚያስገርም ነገር ምንም ባላዩ ጊዜ። ይህስ አምላክ ነው ብለው አሳባቸውን ለወጡ።

[7] በዚያም ስፍራ አጠገብ ፑፕልዮስ የሚሉት የደሴት አለቃ መሬት ነበረ፥ እርሱም እንግድነት ተቀብሎን ሦስት ቀን በፍቅር አሳደረን።

[8] የፑፕልዮስም አባት በንዳድና በተቅማጥ ታሞ ተኝቶ ነበር፤ ጳውሎስም ወደ እርሱ ገብቶ ጸለየለት እጁንም በላዩ ጭኖ ፈወሰው።

[9] ይህም በሆነ ጊዜ የቀሩት ደግሞ በደሴቲቱ ደዌ የነበረባቸው እየመጡ ተፈወሱ፤

[10] በብዙ ክብርም ደግሞ አከበሩን፥ በተነሣንም ጊዜ በመርከብ ላይ የሚያስፈልገንን ነገር አኖሩልን።

[11] ከሦስት ወርም በኋላ በደሴቲቱ ከርሞ በነበረው በእስክንድርያው መርከብ ተነሣን፥ በእርሱም የዲዮስቆሮስ አላማ ነበረበት።

[12] ወደ ሰራኩስም በገባን ጊዜ ሦስት ቀን ተቀመጥን፤

[13] ከዚያም እየተዛወርን ወደ ሬጊዩም ደረስን። ከአንድ ቀን በኋላም የደቡብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜ በሁለተኛው ቀን ወደ ፑቲዮሉስ መጣን።

[14] በዚያም ወንድሞችን አግኝተን በእነርሱ ዘንድ ሰባት ቀን እንድንቀመጥ ለመኑን፤ እንዲሁም ወደ ሮሜ መጣን።

[15] ከዚያም ወንድሞች ስለ እኛ ሰምተው እስከ አፍዩስ ፋሩስና ሦስት ማደሪያ እስከሚባለው ሊቀበሉን ወጡ፥ ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነ ልቡም ተጽናና።

[16] ወደ ሮሜም በገባን ጊዜ ጳውሎስ ከሚጠብቀው ወታደር ጋር ለብቻው ይቀመጥ ዘንድ ተፈቀደለት።

[17] ከሦስት ቀንም በኋላ ጳውሎስ የአይሁድን ታላላቆች ወደ እርሱ ጠራ፤ በተሰበሰቡም ጊዜ እንዲህ አላቸው። ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ሕዝቡን ወይም የአባቶችን ሥርዓት የሚቃወም አንዳች ሳላደርግ፥ ከኢየሩሳሌም እንደ ታሰርሁ በሮማውያን እጅ አሳልፈው ሰጡኝ።

[18] እነርሱም መርምረው ለሞት የሚገባ ምክንያት ስላልነበረብኝ ሊፈቱኝ አሰቡ፤

[19] አይሁድ ግን በተቃወሙ ጊዜ፥ ወደ ቄሣር ይግባኝ እንድል ግድ ሆነብኝ እንጂ ሕዝቤን የምከስበት ነገር ኖሮኝ አይደለም።

[20] ስለዚህም ምክንያት አያችሁና እነግራችሁ ዘንድ ጠራኋችሁ፤ ስለ እስራኤል ተስፋ ይህን ሰንሰለት ለብሻለሁና።

[21] እነርሱም። እኛ ከይሁዳ ስለ አንተ ደብዳቤ አልተቀበልንም፥ ከወንድሞችም አንድ ስንኳ መጥቶ ስለ አንተ ክፉ ነገር አላወራልንም ወይም አልተናገረብህም።

[22] ነገር ግን ስለዚህ ወገን በየስፍራው ሁሉ እንዲቃወሙ በእኛ ዘንድ ታውቆአልና የምታስበውን ከአንተ እንሰማ ዘንድ እንፈቅዳለን አሉት።

[23] ቀንም ቀጥረውለት ብዙ ሆነው ወደ መኖሪያው ወደ እርሱ መጡ፤ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትም እየመሰከረ ስለ ኢየሱስም ከሙሴ ሕግና ከነቢያት ጠቅሶ እያስረዳቸው፥ ከጥዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ይገልጥላቸው ነበር።

[24] እኵሌቶቹም የተናገረውን አመኑ፥ እኵሌቶቹ ግን አላመኑም፤

[25] እርስ በርሳቸውም ባልተስማሙ ጊዜ፥ ጳውሎስ አንዲት ቃል ከተናገረ በኋላ ሄዱ፤ እንዲህም አለ። መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ በኢሳይያስ ለአባቶቻችን።

[26] ወደዚህ ሕዝብ ሂድና። መስማትን ትሰማላችሁና አታስተውሉም፥ ማየትንም ታያላችሁና አትመለከቱም፤

[27] በዓይናቸው እንዳያዩ በጆሮአቸው እንዳይሰሙ በልባቸውም እንዳያስተውሉ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአል ጆሮአቸውም ደንቁሮአል ዓይናቸውንም ጨፍነዋል በላቸው

[28] ሲል መልካም ተናገረ። እንግዲህ ይህ የእግዚአብሔር ደኅንነት ለአሕዛብ እንደ ተላከ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፤ እነርሱ ደግሞ ይሰሙታል።

[29] ይህንም በተናገረ ጊዜ አይሁድ እርስ በርሳቸው እጅግ እየተከራከሩ ሄዱ።

[30] ጳውሎስም በተከራየው ቤት ሁለት ዓመት ሙሉ ተቀመጠ፥ ወደ እርሱም የሚመጡትን ሁሉ ይቀበል ነበር፤

[31] ማንም ሳይከለክለው የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበከ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ ገልጦ ያስተምር ነበር።

የሐዋርያት ሥራ። — Chapters