Skip to content
Opens in a new window

[1] ከዚህም በኋላ ጳውሎስ ከአቴና ወጥቶ ወደ ቆሮንቶስ መጣ።

[2] በወገኑም የጳንጦስ ሰው የሚሆን አቂላ የሚሉትን አንድ አይሁዳዊ አገኘ፤ እርሱም ከጥቂት ጊዜ በፊት ከሚስቱ ከጵርስቅላ ጋር ከኢጣልያ መጥቶ ነበር፥ አይሁድ ከሮሜ ይወጡ ዘንድ ቀላውዴዎስ አዞ ነበርና፤ ወደ እነርሱ ቀረበ፥

[3] ሥራቸውም አንድ ስለ ነበረ በእነርሱ ዘንድ ተቀምጦ በአንድ ላይ ሠሩ፤ ሥራቸው ድንኳን መስፋት ነበረና።

[4] በየሰንበቱም ሁሉ በምኵራብ ይነጋገር ነበር፥ አይሁድንና የግሪክንም ሰዎች ያስረዳ ነበር።

[5] ሲላስና ጢሞቴዎስም ከመቄዶንያ በወረዱ ጊዜ፥ ጳውሎስ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ለአይሁድ እየመሰከረ ለቃሉ ይተጋ ነበር።

[6] ነገር ግን በተቃወሙትና በተሳደቡ ጊዜ፥ ልብሱን እያራገፈ። ደማችሁ በራሳችሁ ነው፤ እኔ ንጹሕ ነኝ ከእንግዲህ ወዲህ ወደ አሕዛብ እሄዳለሁ አላቸው።

[7] ከዚያም ወጥቶ ኢዮስጦስ ወደሚባል እግዚአብሔርን ወደሚያመልክ ሰው ቤት ገባ ቤቱም በምኩራብ አጠገብ ነበረ።

[8] የምኵራብ አለቃ ቀርስጶስም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር በጌታ አመነ፥ ከቆሮንቶስ ሰዎችም ብዙ በሰሙ ጊዜ አምነው ተጠመቁ።

[9] -

[10] ጌታም ሌሊት በራእይ ጳውሎስን። እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፥ ማንም ክፉ ሊያደርግብህ የሚነሣብህ የለምና አትፍራ፥ ነገር ግን ተናገር ዝምም አትበል፤ በዚህ ከተማ ብዙ ሕዝብ አሉኝና አለው።

[11] በመካከላቸውም የእግዚአብሔርን ቃል እያስተማረ ዓመት ከስድስት ወር ተቀመጠ።

[12] ጋልዮስም በአካይያ አገረ ገዥ በነበረ ጊዜ፥ አይሁድ በአንድ ልብ ሆነው በጳውሎስ ላይ ተነሡ፥ ወደ ፍርድ ወንበርም አምጥተው።

[13] ይህ ሕግን ተቃውሞ እግዚአብሔርን ያመልኩት ዘንድ ሰዎችን ያባብላል አሉ።

[14] ጳውሎስም አፉን ሊከፍት ባሰበ ጊዜ፥ ጋልዮስ አይሁድን። አይሁድ ሆይ፥ ዓመፅ ወይም ክፉ በደል በሆነ እንድታገሣችሁ በተገባኝ፤

[15] ስለ ቃልና ስለ ስሞች ስለ ሕጋችሁም የምትከራከሩ ከሆነ ግን፥ ራሳችሁ ተጠንቀቁ እኔ በዚህ ነገር ፈራጅ እሆን ዘንድ አልፈቅድምና አላቸው።

[16] ከፍርድ ወንበርም ፊት አስወጣቸው።

[17] የግሪክ ሰዎችም ሁሉ የምኩራብ አለቃ ሶስቴንስን ይዘው በወንበሩ ፊት መቱት፤ በእነዚህም ነገሮች ጋልዮስ ግድ የለውም ነበር።

[18] ከዚህም በኋላ ጳውሎስ እጅግ ቀን ተቀምጦ ወንድሞቹንም ተሰናብቶ በመርከብ ወደ ሶርያ ሄደ፤ ስለትም ነበረበትና ራሱን በክንክራኦስ ተላጨ፤ ጵርስቅላና አቂላም ከእርሱ ጋር ነበሩ።

[19] ወደ ኤፌሶንም በደረሱ ጊዜ እነዚያን ከዚያ ተዋቸው፥ ራሱ ግን ወደ ምኵራብ ገብቶ ከአይሁድ ጋር ይነጋገር ነበር።

[20] እነርሱም ብዙ ጊዜ እንዲቀመጥላቸው ሲለምኑት እሺ አላለም፤

[21] ነገር ግን ሲሰናበታቸው። የሚመጣውን በዓል በኢየሩሳሌም አደርግ ዘንድ ይገባኛል እግዚአብሔር ቢፈቅድ ግን ወደ እናንተ ደግሞ እመለሳለሁ አላቸው። ከኤፌሶንም በመርከብ ተነሣ።

[22] ወደ ቂሣርያም በደረሰ ጊዜ ወጥቶ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምታ ከሰጠ በኋላ ወደ አንጾኪያ ወረደ።

[23] ጥቂት ቀንም ቆይቶ ወጣ፥ ደቀ መዛሙርትንም ሁሉ እያጸና በገላትያ አገርና በፍርግያ በተራ አለፈ።

[24] በወገኑም የእስክንድርያ ሰው የሆነ ነገር አዋቂ የነበረ አጵሎስ የሚሉት አንድ አይሁዳዊ ሰው ወደ ኤፌሶን ወረደ፤ እርሱም በመጻሕፍት እውቀት የበረታ ነበረ።

[25] እርሱ የጌታን መንገድ የተማረ ነበረ፥ የዮሐንስንም ጥምቀት ብቻ አውቆ በመንፈስ ሲቃጠል ስለ ኢየሱስ ይናገርና በትክክል ያስተምር ነበር።

[26] እርሱም በምኵራብ ገልጦ ይናገር ጀመር። ጵርስቅላና አቂላም በሰሙት ጊዜ፥ ወስደው የእግዚአብሔርን መንገድ ከፊት ይልቅ በትክክል ገለጡለት።

[27] እርሱም ወደ አካይያ ማለፍ በፈቀደ ጊዜ፥ ወንድሞቹ አጸናኑት፥ ይቀበሉትም ዘንድ ወደ ደቀ መዛሙርት ጻፉለት፤ በደረሰም ጊዜ አምነው የነበሩትን በጸጋ እጅግ ይጠቅማቸው ነበር፤

[28] ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ከመጻሕፍት እየገለጠ ለአይሁድ በሁሉ ፊት በጽኑ ያስረዳቸው ነበርና።

የሐዋርያት ሥራ። — Chapters