Skip to content
Opens in a new window

[1] ጳውሎስም ሸንጎውን ትኵር ብሎ ተመልክቶ። ወንድሞች ሆይ፥ እኔ እስከዚች ቀን ድረስ በመልካም ሕሊና ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ኖሬአለሁ አለ።

[2] ሊቀ ካህናቱም ሐናንያ አፉን ይመቱት ዘንድ በአጠገቡ ቆመው የነበሩትን አዘዘ።

[3] በዚያን ጊዜ ጳውሎስ። አንተ በኖራ የተለሰነ ግድግዳ፥ እግዚአብሔር አንተን ይመታ ዘንድ አለው፤ አንተ በሕግ ልትፈርድብኝ ተቀምጠህ ሳለህ ያለ ሕግ እመታ ዘንድ ታዛለህን? አለው።

[4] በአጠገቡ የቆሙትም። የእግዚአብሔርን ሊቀ ካህናት ትሳደባለህን? አሉት።

[5] ጳውሎስም። ወንድሞች ሆይ፥ ሊቀ ካህናት መሆኑን ባላውቅ ነው፤ በሕዝብህ አለቃ ላይ ክፉ ቃል አትናገር ተብሎ ተጽፎአልና አላቸው።

[6] ጳውሎስ ግን እኵሌቶቹ ሰዱቃውያን እኵሌቶቹም ፈሪሳውያን መሆናቸውን አይቶ። ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ፈሪሳዊ የፈሪሳዊም ልጅ ነኝ፤ ስለ ተስፋና ስለ ሙታን መነሣት ይፈርዱብኛል ብሎ በሸንጎው ጮኸ።

[7] ይህንም ባለ ጊዜ በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን መካከል ጥል ሆነ ሸንጎውም ተለያየ።

[8] ሰዱቃውያን። ትንሣኤም መልአክም መንፈስም የለም የሚሉ ናቸውና፤ ፈሪሳውያን ግን ሁለቱን ያምናሉ።

[9] ታላቅ ጩኸትም ሆነ፥ ከፈሪሳውያንም ወገን የሆኑት ጻፎች ተነሥተው። በዚህ ሰው ላይ ምንም ክፉ ነገር አላገኘንበትም፤ መንፈስ ወይስ መልአክ ተናግሮት ይሆን? ብለው ተከራከሩ።

[10] ብዙ ጥልም በሆነ ጊዜ የሻለቃው ጳውሎስን እንዳይገነጣጥሉት ፈርቶ ጭፍሮቹ ወርደው ከመካከላቸው እንዲነጥቁት ወደ ሰፈሩም እንዲያገቡት አዘዘ።

[11] በሁለተኛውም ሌሊት ጌታ በአጠገቡ ቆሞ። ጳውሎስ ሆይ፥ በኢየሩሳሌም ስለ እኔ እንደ መሰከርህ እንዲሁ በሮሜም ትመሰክርልኝ ዘንድ ይገባሃልና አይዞህ አለው።

[12] በጠባም ጊዜ አይሁድ ጳውሎስን እስኪገድሉት ድረስ እንዳይበሉና እንዳይጠጡ በመሐላ ተስማሙ።

[13] ይህንም ሴራ ያደረጉት ሰዎች ከአርባ ይበዙ ነበር፤

[14] እነርሱም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ሽማግሌዎቹ መጥተው። ጳውሎስን እስክንገድል ድረስ ምንም እንዳንቀምስ ተረጋግመን ተማምለናል።

[15] እንግዲህ አሁን እናንተ ከሸንጎው ጋር ሆናችሁ ስለ እርሱ አጥብቃችሁ እንደምትመረምሩ መስላችሁ ወደ እናንተ እንዲያወርደው ለሻለቃው አመልክቱት፤ እኛም ሳይቀርብ እንድንገድለው የተዘጋጀን ነን አሉአቸው።

[16] የጳውሎስ የእኅቱ ልጅ ግን ደባቸውን በሰማ ጊዜ፥ መጥቶ ወደ ሰፈሩ ገባና ለጳውሎስ ነገረው።

[17] ጳውሎስም ከመቶ አለቆች አንዱን ጠርቶ። ይህን ብላቴና ወደ ሻለቃው ውሰድ፥ የሚያወራለት ነገር አለውና አለው።

[18] እርሱም ይዞት ወደ ሻለቃው ወሰደውና። ይህ ብላቴና የሚነግርህ ነገር ስላለው እስረኛው ጳውሎስ ጠርቶ ወደ አንተ እንድወስደው ለመነኝ አለው።

[19] የሻለቃውም እጁን ይዞ ፈቀቅ አለና ለብቻው ሆኖ። የምታወራልኝ ነገር ምንድር ነው? ብሎ ጠየቀው።

[20] እርሱም። አይሁድ ስለ ጳውሎስ ከፊት ይልቅ አጥብቀህ እንደምትመረምር መስለህ፥ ነገ ወደ ሸንጎ ታወርደው ዘንድ ሊለምኑህ ተስማምተዋል።

[21] እንግዲህ አንተ በጅ አትበላቸው፤ እስኪገድሉት ድረስ እንዳይበሉና እንዳይጠጡ ተማምለው ከእነርሱ ከአርባ የሚበዙ ሰዎች ያደቡበታልና፤ አሁንም የተዘጋጁ ናቸው የአንተንም ምላሽ ይጠብቃሉ አለው።

[22] የሻለቃውም። ይህን ነገር ለእኔ ማመልከትህን ለማንም እንዳትገልጥ ብሎ ካዘዘ በኋላ ብላቴናውን አሰናበተው።

[23] ከመቶ አለቆቹም ሁለት ጠርቶ። ወደ ቂሣርያ ይሄዱ ዘንድ ሁለት መቶ ወታደሮችንና ሰባ ፈረሰኞችን ሁለት መቶም ባለ ጦር መሣሪያዎችን ከሌሊቱ በሦስተኛው ሰዓት አዘጋጁ አላቸው።

[24] ጳውሎስንም ወደ አገረ ገዡ ወደ ፊልክስ በደኅና እንዲያደርሱት የሚያስቀምጡበትን ከብት ያዘጋጁ ዘንድ አዘዛቸው።

[25] ደብዳቤም ጻፈ እንዲህ የሚል።

[26] ከቀላውዴዎስ ሉስዮስ ወደ ክቡር አገረ ገዡ ወደ ፊልክስ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን።

[27] ይህን ሰው አይሁድ ይዘው ሊገድሉት ባሰቡ ጊዜ ከጭፍሮቹ ጋር ደርሼ አዳንሁት፥ ሮማዊ እንደ ሆነ አውቄ ነበርና።

[28] የሚከሰስበትንም ምክንያት አውቅ ዘንድ አስቤ ወደ ሸንጎአቸው አወረድሁት፤

[29] በሕጋቸውም ስለ መከራከር እንደ ከሰሱት አገኘሁ እንጂ ለሞት ወይም ለእስራት የሚያደርስ ክስ አይደለም።

[30] በዚህም ሰው አይሁድ ሴራ እንዲያደርጉበት ባመለከቱኝ ጊዜ ያን ጊዜውን ወደ አንተ ሰደድሁት፥ ከሳሾቹንም ደግሞ በፊትህ ይከሱት ዘንድ አዘዝኋቸው። ደኅና ሁን።

[31] ወታደሮቹም እንደ ታዘዙት ጳውሎስን ይዘው በሌሊት ወደ አንቲጳጥሪስ አደረሱት፤

[32] በነገውም ከእርሱ ጋር ይሄዱ ዘንድ ፈረሰኞችን ትተው ወደ ሰፈር ተመለሱ።

[33] እነዚያም ወደ ቂሣርያ ገብተው ደብዳቤውን ለአገረ ገዡ በሰጡ ጊዜ ጳውሎስን ደግሞ በፊቱ አቆሙት።

[34] ካነበበውም በኋላ የወዴት አውራጃ እንደ ሆነ ጠየቀው፤ የኪልቅያ ሰው መሆኑንም ባወቀ ጊዜ።

[35] ከሳሾችህ ደግሞ ሲመጡ እሰማሃለሁ አለው፤ በሄሮድስም ግቢ ውስጥ ይጠብቁት ዘንድ አዘዘ።

የሐዋርያት ሥራ። — Chapters