Skip to content
Opens in a new window

[1] ሁከቱም ከቀረ በኋላ ጳውሎስ ደቀ መዛሙርቱን አስመጥቶ መከራቸው፥ ተሰናብቶአቸውም ወደ መቄዶንያ ይሄድ ዘንድ ወጣ።

[2] ያንም አገር እያለፈ በብዙ ቃል ከመከራቸው በኋላ ወደ ግሪክ አገር መጣ።

[3] በዚያም ሦስት ወር ተቀምጦ ወደ ሶርያ በመርከብ ሊሄድ ባሰበ ጊዜ፥ አይሁድ ሴራ ስላደረጉበት በመቄዶንያ አልፎ ይመለስ ዘንድ ቆረጠ።

[4] የሸኙትም የቤርያው ሱሲጳጥሮስ ከተሰሎንቄ ሰዎችም አርስጥሮኮስና ሲኮንዱስ የደርቤኑም ጋይዮስና ጢሞቴዎስ የእስያ ሰዎችም ቲኪቆስ ጥሮፊሞስም ነበሩ፤

[5] እነዚህም ወደ ፊታችን አልፈው በጢሮአዳ ቆዩን።

[6] እኛ ግን ከቂጣ በዓል ቀን በኋላ ከፊልጵስዩስ በመርከብ ተነሥተን በአምስት ቀን ወደ ጢሮአዳ ወደ እነርሱ ደረስንና በዚያ ሰባት ቀን ተቀመጥን።

[7] ከሳምንቱም በመጀመሪያ ቀን እንጀራ ለመቁረስ ተሰብስበን ሳለን፥ ጳውሎስ በነገው ሊሄድ ስላሰበ ከእነርሱ ጋር ይነጋገር ነበር፥ እስከ መንፈቀ ሌሊትም ነገሩን አስረዘመ።

[8] ተሰብስበንም በነበርንበት ሰገነት እጅግ መብራት ነበረ።

[9] አውጤኪስ የሚሉትም አንድ ጎበዝ በመስኮት ተቀምጦ ታላቅ እንቅልፍ አንቀላፍቶ ነበር፤ ጳውሎስም ነገርን ባስረዘመ ጊዜ እንቅልፍ ከብዶት ከሦስተኛው ደርብ ወደ ታች ወደቀ፥ ሞቶም አነሡት።

[10] ጳውሎስም ወርዶ በላዩ ወደቀ፥ አቅፎም። ነፍሱ አለችበትና አትንጫጩ አላቸው።

[11] ወጥቶም እንጀራ ቆርሶም በላ፤ ብዙ ጊዜም እስኪነጋ ድረስ ተነጋገረ እንዲህም ሄደ።

[12] ብላቴናውንም ደኅና ሆኖ ወሰዱት እጅግም ተጽናኑ።

[13] እኛ ግን ጳውሎስን ከዚያ እንቀበለው ዘንድ ስላለን ወደ መርከብ ቀድመን ሄድንና ወደ አሶን ተነሣን፤ እርሱ በመሬት ይሄድ ዘንድ ስላሰበ እንደዚህ አዞ ነበርና።

[14] በአሶንም ባገኘን ጊዜ ተቀብለነው ወደ ሚጢሊኒ መጣን፤

[15] በማግሥቱም ከዚያ በባሕር ተነሥተን በኪዩ ፊት ለፊት ደረስን፥ በነገውም ወደ ሳሞን ተሻገርን በትሮጊሊዮም አድረን በማግሥቱ ወደ ሚሊጢን መጣን።

[16] ጳውሎስ በእስያ እጅግ እንዳይቀመጥ ኤፌሶንን ይተው ዘንድ ቆርጦ ነበርና ቢቻለውም በዓለ ኀምሳን በኢየሩሳሌም ይውል ዘንድ ይቸኩል ነበርና።

[17] ከሚሊጢንም ወደ ኤፌሶን ልኮ የቤተክርስቲያንን ሽማግሌዎች አስጠራቸው፤

[18] -

[19] ወደ እርሱም በመጡ ጊዜ እንዲህ አላቸው። ወደ እስያ ከገባሁበት ከመጀመሪያ ቀን ጀምሮ፥ በትሕትና ሁሉና በእንባ ከአይሁድም ሴራ በደረሰብኝ ፈተና ለጌታ እየተገዛሁ ዘመኑን ሁሉ ከእናንተ ጋር እንዴት እንደ ኖርሁ እናንተው ታውቃላችሁ፤

[20] -

[21] ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ንስሐንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች እየመሰከርሁ በጉባኤም በየቤታችሁም አወራሁላችሁና አስተማርኋችሁ እንጂ፥ ከሚጠቅማችሁ ነገር አንዳች ስንኳ አላስቀረሁባችሁም።

[22] አሁንም፥ እነሆ፥ እኔ በመንፈስ ታስሬ ወደ ኢየሩሳሌም እሄዳለሁ፥ በዚያም የሚያገኘኝ ምን እንደ ሆነ አላውቅም፤

[23] ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ። እስራትና መከራ ይቆይሃል ብሎ በየከተማው ሁሉ ይመሰክርልኛል።

[24] ነገር ግን ሩጫዬንና ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት እርሱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን መመስከር እፈጽም ዘንድ ነፍሴን በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቆጥራለሁ።

[25] አሁንም፥ እነሆ፥ እኔ የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበክሁ በመካከላችሁ የዞርሁ ሁላችሁ ከእንግዲህ ወዲህ ፊቴን እንዳትዩ አውቃለሁ።

[26] ስለዚህ እኔ ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ እንደ ሆንሁ ዛሬ በዚች ቀን እመሰክርላችኋለሁ።

[27] የእግዚአብሔርን ምክር ሁሉ ነግሬአችኋለሁና፥ ምንም አላስቀረሁባችሁም።

[28] በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።

[29] -

[30] ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ።

[31] ስለዚህ ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሠጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ።

[32] አሁንም ለእግዚአብሔርና ያንጻችሁ ዘንድ በቅዱሳንም ሁሉ መካከል ርስትን ይሰጣችሁ ዘንድ ለሚችል ለጸጋው ቃል አደራ ሰጥቻችኋለሁ።

[33] ከማንም ብር ወይም ወርቅ ወይም ልብስ አልተመኘሁም፤

[34] እነዚህ እጆቼ በሚያስፈልገኝ ነገር ለእኔና ከእኔ ጋር ላሉት እንዳገለገሉ እናንተ ታውቃላችሁ።

[35] እንዲሁ እየደከማችሁ ድውዮችን ልትረዱና እርሱ ራሱ። ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው እንዳለ የጌታን የኢየሱስን ቃል ልታስቡ ይገባችሁ ዘንድ በሁሉ አሳየኋችሁ።

[36] ይህንም ብሎ ተንበርክኮ ከሁላቸው ጋር ጸለየ።

[37] ሁሉም እጅግ አለቀሱ፥ ጳውሎስንም አንገቱን አቅፈው ይስሙት ነበር፤

[38] ይልቁንም። ከእንግዲህ ወዲህ ፊቴን አታዩም ስላላቸው ነገር እጅግ አዘኑ። እስከ መርከብም ድረስ ሸኙት።

የሐዋርያት ሥራ። — Chapters