Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 3:25

[1] አሁንም እናንተ ባለጠጎች ኑ፤ ስለምትመጣባችሁ መከራም ዋይ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ።

[2] እህላችሁ ነቅዞአል፤ ልብሳችሁም በብል ተበልቶአል።

[3] ወርቃችሁና ብራችሁ ዝጎአል፤ ዝገቱም ምስክር ይሆንባችኋል፤ ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላዋል፤ ለኋለኛው ቀንም መዝገብን አከማችታችኋል።

[4] እነሆ፥ ምድራችሁን ያረሱአት የገበሬዎችን ዋጋቸውን ቀማችኋቸው፤ የቀማችኋቸው ገበሬዎችም ይጮሃሉ፤ ያጫጆችም ጩኸት ወደ አሸናፊ እግዚአብሔር ዦሮ ደረሰ።

[5] በምድር ላይ ደስታን አደረጋችሁ፤ ተቀማጠላችሁም፤ ለሚታረድበትም ቀን ፍሪዳን እንደሚያሰባ ልባችሁን አደነደናችሁ።

[6] ጻድቁንም ምንም ሳይቃወማችሁ ተላልፋችሁ ገደላችሁት።

[7] እንግዲህ ወንድሞቻችን ሆይ፥ እነሆ፥ ገበሬ የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናም እስክትቀበል ድረስ እየታገሠ የምድርን ፍሬ እንደሚጠብቅ ጌታችሁ እስከሚመጣባት እስከ ኋለኛይቱ ቀን ድረስ ታገሡ።

[8] የጌታችሁ መምጣት ተቃርባለችና፥ እናንተም እንግዲህ ታገሡ፤ ልቡናችሁንም አጽኑ።

[9] ወንድሞቻችን ሆይ፥ እንዳይፈረድባችሁ፥ እርስ በርሳችሁ አታጕuረምርሙ፤ እነሆ፥ ፈራጅ ከበራችሁ መድረክ ቆሞ ይጠብቃልና።

[10] ወንድሞቻችን ሆይ፥ የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ የሆኑትን፥ በጌታም ስም የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩትን ነቢያትን ተመልከቱ።

[11] እነሆ፥ የታገሡትን ብፁዓን እንላቸዋለን፤ የኢዮብን ትዕግሥት ሰምታችኋል፤ እግዚአብሔርም የፈጸመለትን አይታችኋል፤ የእግዚአብሔር ቸርነቱ ብዙ ነውና፤ ይቅርም ባይ ነውና።

[12] ወንድሞቻችን ሆይ፥ ከሁሉ አስቀድሞ በሰማይም ቢሆን፥ በምድርም ቢሆን፥ በሌላ መሐላም ቢሆን፥ በምንም ፈጽሞ አትማሉ፤ ነገር ግን ከፍርድ በታች እንዳትወድቁ፥ ነገራችሁ አዎን ቢሆን፥ አዎን ይሁን፤ አይደለም ቢሆንም፥ አይደለም ይሁን።

[13] ከእናንተ የሚያዝን ቢኖር ይጸልይ፤ ደስ የሚለውም ቢኖር ይዘምር።

[14] ከእናንተ የታመመ ሰው ቢኖር በቤተ ክርስቲያን ያሉ ቀሳውስትን ይጥራና ይጸልዩለት፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተጸለየበትንም ዘይት ይቅቡት።

[15] የሃይማኖት ጸሎትም ድውዩን ይፈውሰዋል፤ እግዚአብሔርም ያስነሣዋል፤ ኀጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል።

[16] እርስ በርሳችሁ ኀጢአታችሁን ተናዘዙ፤ እንድትድኑም ለወንድሞቻችሁ ጸልዩ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎቱ ብዙ ትረዳለች፤ ግዳጅም ትፈጽማለች።

[17] ኤልያስ እንደ እኛ ሰው ነበር፤ እንደምንታመምም ይታመም ነበር፤ ዝናም እንዳይዘንም ጸሎትን ጸለየ፤ ሦስት ዓመት ከስድስት ወርም በምድር ላይ አልዘነመም።

[18] ዳግመኛም ጸለየ፤ ሰማይም ዝናሙን ሰጠ፤ ምድርም ፍሬዋን አበቀለች።

[19] ወንድሞቻችን ሆይ፥ ከእናንተ ከጽድቅ የሳተ ቢኖር፥ ከኀጢአቱ የመለሰውም ቢኖር፥

[20] ኀጢአተኛውን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ራሱን ከሞት እንደ አዳነ፥ ብዙ ኀጢአቱንም እንደ አስተሰረየ ይወቅ። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንድም የሐዋርያው የቅዱስ ያዕቆብ መልእክት ተፈጸመች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። አሜን።

የያዕቆብ መልእክት። — Chapters