Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 3:42

[1] ወንድሞቻችን ሆይ፥ በክብር ጌታ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለው እምነታችሁ ለሰው ፊት በማድላት አይሁን።

[2] የወርቅ ቀለበት ያደረገና መልካም ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ጉባኤያችሁ ቢገባ፥ ድሃውም ያደፈ ልብስ ለብሶ ቢገባ፥

[3] መልካም ልብስ የለበሰውን አይታችሁ ፥ “አንተማ ና፥ በዚህ በመልካሙ ስፍራ ተቀመጥ ” ብትሉት፥ ድሃውን ግን ፥ “አንተስ በዚያ ቁም፥ ያለዚያም በዚያ ከእግራችን በታች ተቀመጥ ” ብትሉት፥

[4] እንግዲህ እናንተ ራሳችሁ አድልዎ ማድረጋችሁ አይደለምን? በክፉ ዐሳብስ የፈረዳችሁ አይደለምን?

[5] የተወደዳችሁ ወንድሞቻችን ሆይ፥ ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለጠጎች እንዲሆኑ፥ ለሚወዱትም ተስፋ ያደረገላቸውን መንግሥት እንዲወርሱ፥ የዚህን ዓለም ድሆች የመረጣቸው አይደለምን?

[6] እናንተ ግን ድሆችን አቃለላችኋቸው፤ የሚቀሙአችሁ፥ ወደ ሙግትና ወደ ሸንጎም የሚጎትቱአችሁ፥ እነዚያ ባለጠጎች አይደሉምን?

[7] እነርሱ እናንተ የተጠራችሁበትን ገናና ስሙን የሚሰድቡ አይደሉምን?

[8] መጽሐፍ ፥ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” እንደሚል የእግዚአብሔርን ሕግ የምትፈጽሙ ከሆነ መልካም ታደርጋላችሁ።

[9] ለሰው ፊት የምታደሉ ከሆነ ግን ኀጢአትን ታደርጋላችሁ፤ ሕግም እንደ ተላላፊዎች ይዘልፋችኋል።

[10] ሕግን ሁሉ የሚፈጽም፥ ነገር ግን በአንዲቱ የሚሳሳት፥ በሁሉ በደለኛ ይሆናል።

[11] አታመንዝር ያለው እርሱ አትግደል ብሎአልና፤ ባታመነዝር፥ ነገር ግን ብትገድል ሕግን ተላላፊ ትሆናለህ፤

[12] በነጻነት ሕግ ይፈረድባችሁ ዘንድ እንደ አላችሁ መጠን እንዲህ ተናገሩ፤ እንዲህም አድርጉ።

[13] ምሕረትን ለማያደርግ በፍርድ ጊዜ ምሕረት የለውም። ነገር ግን ምሕረትን የሚያደርግ ሰው በፍርድ ቀን ደስ ይለዋል።

[14] ወንድሞቻችን ሆይ፥ እምነት አለኝ፤ ምግባር ግን የለኝም የሚል ሰው ቢኖር፥ ምን ይጠቅመዋል? በውኑ እምነቱ ልታድነው ትችላለችን?

[15] ከወንድሞቻችን፥ ወይም ከእኅቶቻችን፥ የታረዙ ወይም የዕለት ምግብ ያጡ ቢኖሩ፥

[16] ከእናንተም አንዱ ፥ “በሰላም ሂዱ፥ እሳት ሙቁ፥ ትጠግባላችሁም ” ቢላቸው፥ ለችግራቸውም የሚሹትን ባይሰጣቸው ምን ይጠቅማቸዋል?

[17] እንዲሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው።

[18] ነገር ግን አንድ ሰው ፥ “አንተ እምነት አለህ፥ እኔም መልካም ሥራ አለኝ፤ እስቲ ሃይማኖትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፤ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ ” ይላል።

[19] አንተም እግዚአብሔር አንድ እንደ ሆነ ታምናለህ፤ መልካምም ታደርጋለህ፤ እንዲህስ አጋንንትም ያምናሉ፤ ይንቀጠቀጣሉም።

[20] አንተ ሰነፍ ሰው፥ እምነት ያለ ምግባር የሞተች እንደ ሆነች ልታውቅ ትወዳለህን?

[21] አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን ወደ መሠዊያው ባቀረበው ጊዜ፥ በሥራው የጸደቀ አይደለምን?

[22] እምነት ለሥራ ትረዳው እንደ ነበር፥ በሥራውም እምነቱ እንደ መላችና ፍጽምት እንደ ሆነችም ታያለህን?

[23] መጽሐፍ ፥ “አብርሃም በእግዚአብሔር አመነ፤ ጽድቅ ሆኖም ተቈጠረለት ” የሚለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ።

[24] ሰው በሥራ እንደሚጸድቅ፥ በእምነት ብቻም እንዳይደለ ታያለህን?

[25] እንዲሁ ዘማይቱ ረአብ ደግሞ ጕuበኟችን ተቀብላ፥ በሌላ መንገድ ባወጣቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን?

[26] ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ፥ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው።

የያዕቆብ መልእክት። — Chapters