[1] ወንድሞቻችን ሆይ፥ ከመካከላችሁ መምህራን ብዙዎች አይሁኑ፤ ጽኑ ፍርድ እንደምንቀበል ታውቃላችሁና፤
[2] ሁላችን እጅግ እንስታለንና፤ በቃል የማይስት ማንም ቢኖር እርሱ ሥጋውን ሁሉ ደግሞ ሊገታ የሚችል ፍጹም ሰው ነው።
[3] እነሆ፥ ይታዘዙን ዘንድ፥ በፈረሶች በአፋቸው ልጓም እናገባለን፤ አካላቸውንም ሁሉ እንመራለን።
[4] እነሆ፥ መርከቦች ደግሞ አካላቸው ይህን ያህል ታላቅ ሲሆን በነፋስ ኀይል ይነዳሉ፤ ይመለሳሉም፤ ሰውም ይህን ያህል ታናሽ በሆነ መቅዘፍያ ይመልሳቸዋል፤ ወደ ወደደው ወደብም ያደርሳቸዋል።
[5] እንዲሁ ምላስም ትንሽ አካል ናት፤ ታላላቅ ነገርንም ታመጣለች፤ እነሆ እጅግ ትንሽ የሆነች እሳትም ይህን የሚያህል ጫካ ታቃጥላለች።
[6] ምላስም እሳት ናት፤ እነሆ፥ ትንሽ ምላስ በሰውነታችን ውስጥ ዐመፅ የተመላበት ዓለም ናት፤ ሥጋችንን ትበላዋለች፤ ውስጣዊ ሰውነታችንንም ትጠብሰዋለች፤ ከገሃነምም ይልቅ ታቃጥላለች።
[7] የአራዊትና የወፎች፥ የተንቀሳቃሾችና በባሕር ያለ የፍጥረት ወገን ሁሉ ለሰው ይገዛል፤ ተገዝቶአልም።
[8] የሰውን መላስ ግን መግዛት የሚቻለው የለም፤ ክፉ ናት፤ ዐቅምም የላትም፤ የሚገድል መርዝንም የተመላች ናት።
[9] በእርስዋ እግዚአብሔር አብን እናመሰግነዋለን፤ በእርስዋም በአርኣያ እግዚአብሔር የተፈጠረ ሰውን እንረግመዋለን።
[10] ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ፤ ወንድሞቻችን ሆይ፥ እንዲህ አይሁን።
[11] ምንጭስ ከአንድ አፍ የሚጣፍጥንና የሚመርን ውኅ ያመነጫልን?
[12] ወንድሞቻችን ሆይ፥ በለስ ዘይትን፥ ወይስ ወይን በለስን ሊያፈራ ይችላልን? እንዲሁም መራራ ውኅ ጣፋጭ ውኅ አይሆንም፥ ጣፋጭ ውኅም መራራ አይሆንም።
[13] ከእናንተ ብልህና አስተዋይ ማነው? ከጠባዩ ማማር የተነሣ፥ ሥራውን በቅንነትና በማስተዋል ያሳይ።
[14] ነገር ግን መራራ መቀናናትና መከዳዳት በልባችሁ ካለ አትመኩ፤ በእውነትም ላይ አቷሹ።
[15] ይህቺ ጥበብ ከላይ የምትወርድ አይደለችም፤ ነገር ግን የምድር ናት፤ የሥጋም ናት፤ የአጋንንትም ናት።
[16] መቀናናትና መከዳዳት በአሉበት ስፍራ ሁሉ፥ በዚያ ሁከትና ክፉ ሥራ ሁሉ አሉና።
[17] ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፤ በኋላም ታራቂና ገር፥ እሺ ባይ፥ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት።
[18] የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉት ሰዎች በሰላም ይዘራል።