[1] ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከጴጥሮስ፥ በጳንጦስ፥ በገላትያና በቀጰዶቅያ፥ በእስያና በቢታንያ ሀገሮች ለተበተኑ ስደተኟች፥
[2] እግዚአብሔር አስቀድሞ እንዳወቃቸው፥ በመንፈስ ቅዱስም እንደሚቀደሱ፥ ይታዘዙና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ይረጩ ዘንድ፥ ለተመረጡት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።
[3] ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ፥ ለሕያው ተስፋ እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ይመስገን።
[4] የማያረጀውን፥ የማይለወጠውንና የማይጠፋውን፥ በሰማያት ለእኛና ለእናንተ ተጠብቆልን ያለውን ለመውረስ፥
[5] በኋላ ዘመን በሃይማኖት ትገለጥ ዘንድ ለተዘጋጀችው ድኅነት በእግዚአብሔር ኀይል ለተጠበቃችሁት፥
[6] እስከ ዘለዓለም ደስ ይላችኋል፤ ነገር ግን በሚመጣባችሁ ልዩ ልዩ መከራ አሁን ጥቂት ታዝናላችሁ።
[7] በእሳት ከአጠሩት ከጥሩ ወርቅ በሚመረጥ ሃይማኖታችሁ እንደምትቀበሉት መከራ መጠን ኢየሱስ ከርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ በክብር፥ በጌትነትና በምስጋና ትገኛላችሁ።
[8] እርሱም ሳታዩት የምትወዱት ነው፤ እስከ ዛሬም ድረስ አላያችሁትም፤ ነገር ግን ታምኑበታላችሁ፤ አሁንም ፍጻሜ በሌላትና በከበረች ደስታ ደስ ይላችኋል።
[9] በሃይማኖታችሁም ፍጹምነት የነፍሳችሁን ድኅነት ታገኛላችሁ።
[10] ለእናንተም ስለሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩ ነቢያት የመረመሩአትና የፈለጉአት መድኀኒት ናት።
[11] በእነርሱም የነበረ የክርስቶስ መንፈስ ስለ ክርስቶስ መከራ፥ ከእርሱም በኋላ ስለሚመጣው ክብር፥ አስቀድሞ እየመሰከረ በምን ወይም እንዴት ባለ ዘመን እንዳመለከተ ይመረምሩ ነበር።
[12] ለእነርሱም ከሰማይ በተላከ በመንፈስ ቅዱስ ወንጌልን የሰበኩላችሁ ሰዎች አሁን በነገሩአችሁ ነገር እናንተን እንጂ ራሳቸውን እንዳላገለገሉ ተገለጠላቸው። ይህንም ነገር መላእክቱ ሊመለከቱ ይመኛሉ።
[13] ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና ነቅታችሁ ኑሩ፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ።
[14] እንደሚታዘዙ ልጆች ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ክፉ ምኟት አትከተሉ።
[15] ነገር ግን የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እንዲሁ እናንተም በአካሄዳችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ።
[16] “እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ” የሚል ተጽፎአልና።
[17] ለሰው ፊትም ሳያዳላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርድ አብን የምትጠሩት ከሆነ፥ በሕይወታችሁ ዘመን ሁሉ በፍርሀት ኑሩ።
[18] ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከማይረባና ከማይጠቅም ሥራችሁ የተቤዣችሁ በሚጠፋ በወርቅ ወይም በብር እንዳይደለ ታውቃላችሁ።
[19] ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክርስቶስ ክቡር ደም ነው እንጂ።
[20] ዓለም ሳይፈጠር የታወቀ፥ በኋላ ዘመን ስለ እናንተ ተገለጠ።
[21] ከሙታን ለይቶ በአስነሣው፥ ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ ቃል ያመናችሁ፥ አሁንም እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሁን።
[22] ሳትጠራጠሩ በፍጹም ልቡናችሁ ወንድሞቻችሁን ትወድዱ ዘንድ፥ ለእውነት በመታዘዝ ሰውነታችሁን አንጹ፤ እርስ በእርሳችሁም ተፋቀሩ።
[23] ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፤ በሕያውና ለዘለዓለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ።
[24] “ሥጋ የለበሰ ሁሉ እንደ ሣር፥ ክብሩም ሁሉ እንደ ሣር አበባ ነውና፤ ሣሩ ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል።
[25] የእግዚአብሔር ቃል ግን ለዘለዓለም ይኖራል።” በወንጌልም የተሰበከላችሁ ቃል ይህ ነው።