Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 3:28

[1] ክርስቶስ ስለ እኛ በሥጋው ከተሰቀለ፥ እናንተም ይህቺን ዐሳብ ጋሻ አድርጋችሁ ኑሩ፤ በሥጋዉ መከራ የተቀበለ ከኀጢአት ድኖአልና።

[2] ከእንግዲህ ወዲህ በሥጋው ከሕይወቱ ዘመን የቀረውን፥ በሰው ፈቃድ ሳይሆን በእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲፈጽም ነው እንጂ።

[3] የአሕዛብን ፈቃድ ፥ ዝሙትንና ምኟትን፥ ስካርንና ወድቆ ማደርን፥ ያለ ልክ መጠጣትንና ጣዖት ማምለክን ያደረጋችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃችኋልና።

[4] እንግዲህ ወደዚህ ሥራ እንዳትሮጡ ዕወቁ፤ ከዚች ጎዳናና መጠን ከሌለው ከዚያ ሥራም ተለዩ፤ እነሆ፥ ከእነርሱም መካከል ሰዎች ስለ እናንተ ያደንቃሉ፤ በዚያም በቀድሞው ሥራ ሳትተባበሩአቸው ሲያዩአችሁ ይሰድቡአችኋል።

[5] እነርሱም በሕያዋንና በሙታን ይፈርድ ዘንድ ተዘጋጅቶ ላለው መልስ ይሰጣሉ።

[6] ስለዚህም በሥጋቸው በሰው ሕግ እንዲቀጡ፥ በነፍሳቸውም በእግዚአብሔር ሕግ እንዲድኑ ለሙታን ወንጌልን ሰበኩላቸው።

[7] የሁሉ ፍጻሜው ቀርቦአልና ልባችሁን አንጹ፤ ለጸሎትም ትጉ።

[8] ከሁሉ አስቀድሞ በፍጹም ልቡናችሁ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ ፍቅር ኀጢአትን ሁሉ ይሸፍናልና።

[9] ሳታንጐራጕuሩ እርስ በርሳችሁ እንግዳ መቀበልን ውደዱ።

[10] ሁላችሁም በየራሳችሁ ከእግዚአብሔር የተሰጣችሁን ዕድል እንደ ተቀበላችሁ መጠን እንደ ደግ መጋቢ አገልግሉ፤ ለእያንዳንዱ ከእግዚአብሔር ስጦታው እየራሱ ነውና።

[11] የሚያስተምርም፥ እንደ እግዚአብሔር ቃል ያስተምር፥ የሚያገለግልም እግዚአብሔር በሚሰጠው ኀይል ያገልግል፤ ክብርና ኀይል እስከ ዘለዓለም ድረስ ገንዘቡ በሚሆን በኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር በሁሉ ነገር ይመሰገን ዘንድ።

[12] ወዳጆች ሆይ፥ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ፥ ድንቅ ነገር እንደመጣባችሁ አትደነቁ።

[13] ነገር ግን በጌትነቱ በተገለጠ ጊዜ ደግሞ ደስ ብሎአችሁ ኀሤት እንድታደርጉ ክርስቶስን በመከራ ትመስሉት ዘንድ ደስ ይበላችሁ።

[14] ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ ብፁዓን ናችሁ፤ የእግዚአብሔር የኀይሉና የክብሩ መንፈስ በእናንተ ያርፋልና።

[15] ከእናንተ መካከል እንደ ነፍሰ ገዳይ፤ ወይም እንደ ሌባ፥ ወይም እንደ ክፉ አድራጊ፥ ወይም በሌሎች ጉዳይ እንደሚገባ ሆኖ መከራ የሚቀበል አይኑር።

[16] የክርስቲያን ወገን እንደ መሆኑ መከራን ቢቀበል ግን ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር።

[17] በእግዚአብሔር ቤተ ሰቦች ፍርድ የሚጀመርበት ጊዜ ደርሶአልና፤ መጀመሩ ከእኛ ወገን ከሆነ ግን ለእግዚአብሔር ወንጌል ለማይታዘዙ ሰዎች ፍጻሜአቸው ምን ይሆን?

[18] ጻድቅ በጭንቅ የሚድን ከሆነ ኀጢአተኛና ዐመፀኛ በየት ይገለጥ ዘንድ አለው?

[19] እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መከራን የሚቀበሉ ሰዎችም መልካም ሥራ በመሥራት ለታመነ ፈጣሪ ነፍሳቸውን አደራ ይስጡ።

የጴጥሮስ መልእክት። — Chapters