Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 3:01

[1] ጌቶች ሆይ፥ ለአገልጋዮቻችሁ ትክክለኛውን አድርጉላቸው፤ እውነትንም ፍረዱ፤ በሰማይ ጌታ እንዳላችሁ ታውቃላችሁና። ስለ ወንጌል መስፋፋት መጸለይ እንደሚገባ

[2] በምስጋና እየተጋችሁ ለጸሎት ፅሙዳን ሁኑ።

[3] ስለ እርሱ የታሰርሁለትን የእግዚአብሔርን ምሥጢር እንድንናገር፥ እግዚአብሔር የቃሉን በር ይከፍትልን ዘንድ ለእኛም ደግሞ ጸልዩልን፤ ለምኑልንም፤

[4] ልናገርም እንደሚገባኝ እገልጠው ዘንድ ጸልዩልኝ።

[5] ዘመኑን እየዋጃችሁ ከሃይማኖት ወደ ተለዩ ሰዎች በማስተዋል ሂዱ።

[6] ለእያንዳንዱ እንዴት እንደምትመልሱ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ በጨው እንደ ተቀመመ በጸጋ ይሁን።

[7] የተወደደ ወንድማችንና የታመነ አገልጋይ፥ በጌታ ሥራም ተባባሪያችን የሆነ ቲኪቆስ የእኔን ዜና ይነግራችኋል።

[8] ስለዚህ ሥራ ወደ እናንተ የላክሁት ዜናዬን ታውቁ ዘንድ፥ ልባችሁንም ያጽናና ዘንድ ነው።

[9] ወገናችሁ ከሆነው ከምንወደውና ከታመነው ወንድማችን ከአናሲሞስ ጋር፥ እነርሱ ሥራችንንና ያለንበትን ያስረዱአችኋል።

[10] ከእኔ ጋር የተማረከው አርስጥሮኮስ፥ ወደ እናንተ በሚመጣ ጊዜ ትቀበሉት ዘንድ ስለ እርሱ ያዘዝኋችሁ የበርናባስ የአባቱ ወንድም ልጅ ማርቆስም፥

[11] ኢዮስጦስ የተባለ ኢያሱም፥ ከግዙራን ሰዎች ወገን የሚሆኑ እነዚህ ሰላም ይሏችኋል። በእግዚአብሔር መንግሥት ሥራ ረዳቶቼ እነዚህ ብቻ ናቸው፤ እነርሱም እኔን አጽናንተውኛል።

[12] ከእናንተ ወገን የሚሆን ኤጳፍራስም ሰላም ይላችኋል፥ እርሱ የክርስቶስ አገልጋይ ነው፤ እግዚአብሔር በሚወደው ነገር ሁሉ ምሉኣንና ፍጹማን እንድትሆኑ፥ ስለ እናንተ ዘወትር ይጸልያል፤ ይማልዳልም።

[13] እጅግ እንደሚወዳችሁና ስለ እናንተ በሎዶቅያና በኢያራ ከተማ ስላሉትም እንደሚቈረቈር እኔ ምስክሩ ነኝ።

[14] ወዳጃችን ባለ መድኃኒቱ ሉቃስም ሰላም ብሎአችኋል፤ ዴማስም ሰላም ይላችኋል።

[15] በሎዶቅያ ላሉት ወንድሞቻችንና ለንምፋን፥ በቤቱም ላለች ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልኝ።

[16] ይህችን መልእክት እናንተ አንብባችሁ፥ በቤተ ክርስቲያን ያነብቡአት ዘንድ ወደ ሎዶቅያ ላኩአት፤ ዳግመኛም እናንተ ከሎዶቅያ የጻፍኋትን መልእክት አንብቡአት።

[17] አክርጳንም “ከእግዚአብሔር የተሾምህባትን መልእክትህን እንድትፈጽማት ተጠንቀቅ ” በሉት።

[18] እኔ ጳውሎስ በእጄ ጽፌ ሰላም አልኋችሁ፤ እስራቴን አስቡ፤ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን። በሮሜ ተጽፋ በቲኪቆስ እጅ ወደ ቈላስይስ ሰዎች የተላከችው መልእክት ተፈጸመች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። አሜን።

ወደ ቈላስይስ ሰዎች። — Chapters