[1] ስለ እናንተ እና በሎዶቅያ ስላሉ፥ ፊቴንም በሥጋ ስላላዩት ምእመናን ሁሉ ምን ያህል እንደምጋደል ልታውቁ እወዳለሁ።
[2] ይኸውም ልቡናቸው ደስ ይለው ዘንድ፥ ትምህርታቸውም በማወቅ፥ በፍቅርና ፍጹምነት ባለው ባለጸግነት፥ በጥበብና በሃይማኖት፥ ስለ ክርስቶስም የሆነውን የእግዚአብሔርን ምክር በማወቅ ይጸና ዘንድ ነው።
[3] የተሰወረ የጥበብና የምክር መዝገብ ሁሉ በእርሱ ዘንድ አለ።
[4] ይህንም የምላችሁ በሚያባብል ነገር የሚያስታችሁ እንዳይኖር ነው።
[5] እኔ በሥጋ ከእናንተ ዘንድ ባልኖርም እንኳን፥ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝ፤ እነሆ ጠባያችሁንና ሥርዐታችሁን፥ በክርስቶስም ያለ የእምነታችሁን ጽናት ስለ አየሁ ደስ ይለኛል።
[6] እንግዲህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ተቀበላችሁት፥ በእርሱ ተመላለሱ።
[7] በእርሱ ተመሥርታችሁ ታነጹ፤ በምስጋናው ትበዙ ዘንድ፥ በተማራችሁት ሃይማኖት ጽኑ።
[8] ለዚህ ዓለም ስሕተት፥ በክርስቶስ ሕግ ያይደለ፥ በሰው ሠራሽ ሥርዐት ለከንቱ የሚያታልሉ ሰዎች በነገር ማራቀቅ እንዳያታልሉአችሁ፥ ተጠንቀቁ።
[9] በእርሱ ፍጹም መለኮቱ በሥጋ ተገልጦ ይኖራልና።
[10] እናንተም በእርሱ ፍጹማን ሁኑ፤ እርሱ ለአለቅነት ሁሉና ለሥልጣን ሁሉ ራስ ነውና።
[11] የኀጢአትን ሰውነት ሸለፈት በመግፈፍ በክርስቶስ መገረዝ በሰው እጅ የአልተደረገ መገረዝን በእርሱ ሆናችሁ ተገረዛችሁ።
[12] በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችኋል፤ በእርስዋም ከሙታን ለይቶ ባስነሣው በእግዚአብሔር ረዳትነትና በሃይማኖት ከእርሱ ጋር ተነሥታችኋል።
[13] እናንተም በኀጢአታችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን ነበራችሁና፥ ከእርሱ ጋር ሕያዋን አደረጋችሁ፤ ኀጢአታችሁንም ሁሉ ይቅር አላችሁ።
[14] ከባላጋራችን የተነሣ በትእዛዝ የተጻፈውን የዕዳችንን ደብዳቤ ደመሰሰልን፤ ከመካከላችንም አራቀው፤ በመስቀሉም ቸነከረው።
[15] አለቆችንና ገዢዎችን በመግፈፉ በግልጥ አሳያቸው፤ ራቁቱን በመሆኑም አሳፈራቸው።
[16] እንግዲህ በመብልም ቢሆን፥ በመጠጥም ቢሆን፥ በልዩ ልዩ በዓላትም ቢሆን፥ በመባቻም ቢሆን፥ በሰንበትም ቢሆን የሚነቅፋችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ።
[17] ይህ ሁሉ ይመጣ ዘንድ ላለው ጥላ ነውና። አካሉ ግን የክርስቶስ ነው።
[18] በመታለልና ራስን ዝቅ በማድረግ ለመላእክት አምልኮ ትታዘዙ ዘንድ ወድዶ፥ በአላየውም በከንቱ የሥጋው ምክር እየተመካ የሚያሰንፋችሁ አይኑር።
[19] ሥጋ ሁሉ ጸንቶ በሚኖርበት፥ በሥርና በጅማትም በሚስማማበት፥ በእግዚአብሔርም በሚያድግበትና በሚጸናበት፥ በሚሞላበትም በራስ አይጸናም።
[20] ከዚህ ዓለም ኑሮ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ እንደገና በዓለም እንደሚኖሩ ሰዎች እንዴት ትሠራላችሁ?
[21] እንዴትስ ይህን አትዳስስ፥ ይህን አትንካ፥ ይህንም አትቅመስ ይሉአችኋል?
[22] ይህ ሁሉ እንደ ሰው ትእዛዝና ትምህርት ለጥፋት ነውና።
[23] ይህም ስለ ልብ ትሕትናና እግዚአብሔርንም ስለ መፍራት፥ ለሥጋ ስለ አለማዘን ጥበብን ይመስላል፤ ነገር ግን ከሥጋ በላይ ነው እንጂ ምንም ክብር የለውም።