Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 4:31

[1] በእግዚአብሔር ፈቃድ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከጳውሎስና ከወንድማችን ከጢሞቴዎስ፥

[2] በቈላስይስ ላሉ ቅዱሳንና በኢየሱስ ክርስቶስ ላመኑ ወንድሞቻችን፥ ከአባታችን ከእግዚአብሔር ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስም ሰላምና ጸጋ ለእናንተ ይሁን።

[3] የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት እግዚአብሔርን ዘወትር ስለ እናንተ እናመሰግነዋለን።

[4] በኢየሱስ ክርስቶስ ማመናችሁንና ቅዱሳንንም ሁሉ መውደዳችሁን ከሰማንበት ጊዜ ጀምሮ፥ ስለ እናንተ እንጸልያለን።

[5] የእውነት ቃል በሆነው በወንጌል ትምህርት፥ አስቀድሞ ስለ ሰማችሁት፥ በሰማይ ስለ ተዘጋጀላችሁ ተስፋችሁም እንጸልያለን።

[6] ይህም ወደ እናንተ የደረሰውን የእግዚአብሔርን ጸጋ በእውነት ከሰማችሁበትና ከአያችሁበት ቀን ጀምሮ በመላው ዓለም ያድግና ያፈራ ዘንድ ነው።

[7] ስለ እናንተ የሚላክ በክርስቶስ የታመነ፥ የእኛም ወንድማችንና አገልጋያችን ከሚሆን ከኤጳፍራስ ተምራችኋል።

[8] እርሱም በመንፈስ መዋደዳችሁን ነገረን።

[9] ስለዚህም እኛ ዜናችሁን ከሰማን ጀምሮ፥ በፍጹም ጥበብና በፍጹም መንፈሳዊ ምክር የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማወቅን ትፈጽሙ ዘንድ፥ ስለ እናንተ መጸለይንና መለመንን አልተውንም።

[10] ወደ እግዚአብሔር በሚገባችሁ ትሄዱ ዘንድ፥ በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ፥ እግዚአብሔርንም በማወቅ እያደጋችሁ፥ በሁሉ ደስ ታሰኙት ዘንድ።

[11] በፍጹም ኀይል፥ በክብሩ ጽናት፥ በፍጹም ትዕግሥት፥ በተስፋና በደስታም ጸንታችሁ።

[12] በብርሃን ቅዱሳን ለሚታደሉት ርስት የበቃን ያደረገንን እግዚአብሔር አብን አመስግኑት።

[13] ከጨለማ አገዛዝ አዳነን፤ ወደ ተወደደው ልጁ መንግሥትም መለሰን።

[14] ድኅነትን ያገኘንበት፥ ኀጢአታችንም የተሠረየበት ነው።

[15] ይኸውም የማይታይ እግዚአብሔርን የሚመስለው፥ ከፍጥረቱ ሁሉ በላይ የሆነ በኵuር ነው።

[16] በእርሱ ቃልነት እግዚአብሔር ሁሉን ፈጥሮአልና በሰማይ ያለውን፥ በምድርም ያለውን፥ የሚታየውንና የማይታየውን፥ መናብርትም ቢሆኑ፥ አጋእዝትም ቢሆኑ፥ መኳንንትም ቢሆኑ፥ ቀደምትም ቢሆኑ፥ ሁሉን በእርሱ ቃልነት ፈጥሮአቸዋልና፤ ሁሉም በእጁ ሆነ፤ ሁሉም በእርሱ ለእርሱ ተፈጠረ፤

[17] እርሱ ከሁሉ አስቀድሞ ነበረ፤ ሁሉም በእርሱ ጸና።

[18] እርሱ የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ በኵuር እርሱ ለሁሉ ራስ ይሆን ዘንድ ከሙታን ሁሉ አስቀድሞ ተነሥቶአልና።

[19] ሁሉ በእርሱ ፍጹም ሆኖ ይኖር ዘንድ፥ ወዶአልና።

[20] ሁሉንም በእርሱ ይቅር ይለው ዘንድ በመስቀሉ ባፈሰሰው ደም በምድርና በሰማያት ላሉ ሰላምን አደረገ።

[21] እናንተም ቀድሞ በአሳባችሁና በክፉ ሥራችሁ ከእግዚአብሔር የተለያችሁና ጠላቶች ነበራችሁ።

[22] አሁን ግን በፊቱ ለመቆም የተመረጣችሁና ንጹሓን፥ ቅዱሳንም ያደርጋችሁ ዘንድ በሥጋው ሰውነት በሞቱ ይቅር አላችሁ።

[23] እንግዲህ ከሰማችሁት ከሰማይ በታች በመላው ዓለም ከተሰበከው እኔ ጳውሎስም አዋጅ ነጋሪና መልእክተኛ ሆኜ ከተሾምሁለት፥ ከወንጌል ትምህርት ተስፋ የመሠረታችሁ አቅዋም ሳይናወጥ ጨክናችሁ በሃይማኖት ብትጸኑ፥

[24] አሁንም በመከራዬ ደስ ይለኛል፤ አካሉ ስለ ሆነች ስለ ቤተ ክርስቲያን፥ ከክርስቶስ መከራ ጥቂቱን በሥጋዬ እፈጽማለሁ።

[25] ስለ እናንተ በሰጠኝ በእግዚአብሔር ሥርዐት እኔ መልእክተኛ ሆኜ የተሾምሁላት።

[26] እግዚአብሔር የተናገረውን፥ ዓለም ሳይፈጠር፥ ሰውም ሳይፈጠር ተሰውሮ የነበረውን ምክሩን እፈጽም ዘንድ።

[27] ዛሬ ግን እግዚአብሔር የዚህን ምክር የክብር ባለጸግነት በአሕዛብ ላይ እንዲገልጽላቸው ለፈቀደላቸው ለቅዱሳን ተገለጠላቸው፤ የምንከብርበት አለኝታችን በእናንተ አድሮ ያለ ክርስቶስ ነውና።

[28] እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን ፍጹም የሚሆነውን ሰው እናቀርበው ዘንድ፥ እኛ የምናስተምርለት፥ ሰውን ሁሉ ወደ እርሱ የምንጠራለትና የምንገሥጽለት፥ ሥራውንም በጥበብ ሁሉ የምንናገርለት ነው።

[29] በኀይሉ እንደሚረዳኝ እንደ ረድኤቱ መጠን ስለ እርሱ እደክማለሁ፤ እጋደላለሁም።

ወደ ቈላስይስ ሰዎች። — Chapters