Skip to content
Opens in a new window

[1] ስለ ጻፋችሁልኝስ ነገር፥ ከሴት ጋር አለመገናኘት ለሰው መልካም ነው።

[2] ነገር ግን ስለ ዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ለራሱ ሚስት ትኑረው ለእያንዳንዲቱ ደግሞ ለራስዋ ባል ይኑራት።

[3] ባል ለሚስቱ የሚገባትን ያድርግላት፥ እንደዚሁም ደግሞ ሚስቲቱ ለባልዋ።

[4] ሚስት በገዛ ሥጋዋ ላይ ሥልጣን የላትም፥ ሥልጣን ለባልዋ ነው እንጂ፤ እንዲሁም ደግሞ ባል በገዛ ሥጋው ላይ ሥልጣን የለውም፥ ሥልጣን ለሚስቱ ነው እንጂ።

[5] ለጸሎት ትተጉ ዘንድ ተስማምታችሁ ለጊዜው ካልሆነ በቀር፥ እርስ በርሳችሁ አትከላከሉ፤ ራሳችሁን ስለ አለመግዛት ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ ደግሞ አብራችሁ ሁኑ።

[6] ዳሩ ግን ይህን እንደ ፈቃድ እላለሁ እንጂ እንደ ትእዛዝ አይደለም።

[7] ሰው ሁሉ እንደ እኔ ሊሆን እወዳለሁና፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ከእግዚአብሔር ለራሱ የጸጋ ስጦታ አለው፥ አንዱ እንደዚህ ሁለተኛውም እንደዚያ።

[8] ላላገቡና ለመበለቶች ግን እላለሁ። እንደ እኔ ቢኖሩ ለእነርሱ መልካም ነው፤

[9] ነገር ግን በምኞት ከመቃጠል መጋባት ይሻላልና ራሳቸውን መግዛት ባይችሉ ያግቡ።

[10] -

[11] ሚስትም ከባልዋ አትለያይ፥ ብትለያይ ግን ሳታገባ ትኑር ወይም ከባልዋ ትታረቅ፥ ባልም ሚስቱን አይተዋት ብዬ የተጋቡትን አዛቸዋለሁ፥ እኔ ግን አላዝም፥ ጌታ እንጂ።

[12] ሌሎችንም እኔ እላለሁ፥ ጌታም አይደለም፤ ከወንድሞች ወገን ያላመነች ሚስት ያለችው ቢኖር እርስዋም ከእርሱ ጋር ልትቀመጥ ብትስማማ፥ አይተዋት፤

[13] ያላመነ ባል ያላት ሚስትም ብትኖር ይህ ከእርስዋ ጋር ሊቀመጥ ቢስማማ፥ አትተወው።

[14] ያላመነ ባል በሚስቱ ተቀድሶአልና፥ ያላመነችም ሚስት በባልዋ ተቀድሳለች፤ አለዚያ ልጆቻችሁ ርኵሳን ናቸው፤ አሁን ግን የተቀደሱ ናቸው።

[15] የማያምን ግን ቢለይ ይለይ፤ ወንድም ቢሆን ወይም እኅት እንዲህ በሚመስል ነገር አይገዙም፤ እግዚአብሔር ግን በሰላም ጠርቶናል።

[16] አንቺ ሴት፥ ባልሽን ታድኚ እንደ ሆንሽ ምን ታውቂአለሽ? ወይስ አንተ ሰው፥ ሚስትህን ታድን እንደ ሆንህ ምን ታውቃለህ?

[17] ብቻ ለእያንዳንዱ እግዚአብሔር እንደ ከፈለለት እያንዳንዱም እግዚአብሔር እንደ ጠራው እንዲሁ ይመላለስ። እንዲሁም በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እደነግጋለሁ።

[18] ማንም ተገርዞ ሳለ ተጠርቶ እንደ ሆነ፥ ወደ አለመገረዝ አይመለስ፤ ማንም ሳይገረዝ ተጠርቶ እንደ ሆነ አይገረዝ።

[19] መገረዝ ቢሆን አለመገረዝም ቢሆን ከንቱ ነው፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መጠበቅ ነው እንጂ።

[20] እያንዳንዱ በተጠራበት መጠራት እንደዚሁ ይኑር።

[21] ባሪያ ሆነህ ተጠርተህ እንደ ሆነ አይገድህም፤ አርነት ልትወጣ ቢቻልህ ግን አርነትን ተቀበል።

[22] ባሪያ ሆኖ በጌታ የተጠራ የጌታ ነጻ ነውና፤ እንዲሁም ነጻ ሆኖ የተጠራ የክርስቶስ ባሪያ ነው።

[23] በዋጋ ተገዝታችኋል፤ የሰው ባሪያዎች አትሁኑ።

[24] ወንድሞች ሆይ፥ እያንዳንዱ በተጠራበት እንደዚሁ ሆኖ በእግዚአብሔር ዘንድ ይኑር።

[25] ስለ ደናግልም የጌታ ትእዛዝ የለኝም፥ ነገር ግን የታመንሁ እሆን ዘንድ ከጌታ ምሕረትን የተቀበልሁ እንደ መሆኔ ምክር እመክራለሁ።

[26] እንግዲህ ስለ አሁኑ ችግር ይህ መልካም ይመስለኛል፤ ሰው እንዲህ ሆኖ ቢኖር መልካም ነው።

[27] በሚስት ታስረህ እንደ ሆንህ መፋታትን አትሻ፤ በሚስት አልታሰርህ እንደ ሆንህ ሚስትን አትሻ።

[28] ብታገባ ግን ኃጢአት አትሠራም ድንግሊቱም ብታገባ ኃጢአት አትሠራም፤ ነገር ግን እንዲህ በሚያደርጉ በሥጋቸው ላይ መከራ ይሆንባቸዋል፥ እኔም እራራላችሁ ነበር።

[29] ዳሩ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፥

[30] የሚያለቅሱም እንደማያለቅሱ፥ ደስ የሚላቸውም ደስ እንደማይላቸው፥

[31] የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና።

[32] ነገር ግን ያለ አሳብ ልትኖሩ እወዳለሁ። ያላገባው ጌታን እንዴት ደስ እንዲያሰኘው የጌታን ነገር ያስባል፤

[33] ያገባው ግን ሚስቱን እንዴት ደስ እንዲያሰኛት የዓለምን ነገር ያስባል፥ ልቡም ተከፍሎአል።

[34] ያልተጋባች ሴትና ድንግል በሥጋም በነፍስም እንዲቀደሱ የጌታን ነገር ያስባሉ፤ የተጋባች ግን ባልዋን እንዴት ደስ እንድታሰኘው የዓለምን ነገር ታስባለች።

[35] ይህንም ለራሳችሁ ጥቅም እላለሁ፤ በአገባብ እንድትኖሩ ሳትባክኑም በጌታ እንድትጸኑ ነው እንጂ ላጠምዳችሁ ብዬ አይደለም።

[36] ዳሩ ግን ማግባት ወደሚገባው ዕድሜ በደረሰ ጊዜ ስለ ድንግልናው ያፈረ ሰው ቢኖር፥ የወደደውን ያድርግ፤ ኃጢአት የለበትም፤ ይጋቡ።

[37] ሳይናወጥ በልቡ የጸና ግን ግድ የለበትም፥ የወደደውን እንዲያደርግ ተፈቅዶለታል፤ ድንግልናውንም በልቡ ይጠብቅ ዘንድ ቢጸና፥ መልካም አደረገ።

[38] እንዲሁም ድንግልን ያገባ መልካም አደረገ ያላገባም የተሻለ አደረገ።

[39] ሴት ባልዋ በሕይወት ሳለ የታሰረች ናት፤ ባልዋ ቢሞት ግን በጌታ ይሁን እንጂ የወደደችውን ልታገባ ነጻነት አላት።

[40] እንደ ምክሬ ግን እንዳለች ብትኖር ደስተኛ ናት፤ እኔም ደግሞ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ያለ ይመስለኛል።

ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1 — Chapters