[1] ለቅዱሳንም ገንዘብን ስለ ማዋጣት፥ ለገላትያ አብያተ ክርስቲያናት እንደ ደነገግሁት እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ።
[2] እኔ ስመጣ ይህ የገንዘብ ማዋጣት ያን ጊዜ እንዳይሆን፥ ከእናንተ እያንዳንዱ በየሳምንቱ በፊተኛው ቀን እንደ ቀናው መጠን እያስቀረ በቤቱ ያስቀምጥ።
[3] ስመጣም ማናቸውም ቢሆኑ የታመኑ የሚመስሉአችሁ ሰዎች ቸርነታችሁን ወደ ኢየሩሳሌም ያደርሱ ዘንድ ደብዳቤ ሰጥቼ እልካቸዋለሁ፤
[4] እኔ ደግሞ ልሄድ የሚገባኝ ብሆን ከእኔ ጋር አብረው ይሄዳሉ።
[5] በመቄዶንያም ሳልፍ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ በመቄዶንያ አድርጌ አልፋለሁና፤
[6] እናንተም ወደምሄድበት ወደ ማናቸውም ስፍራ በጉዞዬ እንድትረዱኝ ምናልባት በእናንተ ዘንድ እቆይ ወይም እከርም ይሆናል።
[7] አሁን እግረ መንገዴን ሳልፍ ልጎበኛችሁ አልወድምና፤ ጌታ ቢፈቅደው የሆነውን ዘመን በእናንተ ዘንድ ልሰነብት ተስፋ አደርጋለሁና።
[8] በኤፌሶን ግን እስከ በዓለ ኀምሳ ድረስ እሰነብታለሁ።
[9] ሥራ የሞላበት ትልቅ በር ተከፍቶልኛልና ተቃዋሚዎችም ብዙ ናቸው።
[10] ጢሞቴዎስም የመጣ እንደ ሆነ በእናንተ ዘንድ ያለ ፍርሃት እንዲኖር ተጠንቀቁ፤ እንደ እኔ ደግሞ የጌታን ሥራ ይሠራልና፤ እንግዲህ ማንም አይናቀው።
[11] ነገር ግን ከወንድሞቹ ጋር እጠብቀዋለሁና ወደ እኔ ይመጣ ዘንድ በሰላም በጉዞው እርዱት።
[12] ስለ ወንድማችን ስለ አጵሎስ ግን ከወንድሞቹ ጋር ወደ እናንተ ሊሄድ እጅግ አድርጌ ለምኜው ነበር፤ ዛሬም ለመምጣት ከቶ ፈቃድ አልነበረውም፥ ሲመቸው ግን ይመጣል።
[13] ንቁ፥ በሃይማኖት ቁሙ፥ ጎልምሱ ጠንክሩ።
[14] በእናንተ ዘንድ ሁሉ በፍቅር ይሁን።
[15] ወንድሞች ሆይ፥ የእስጢፋኖስ ቤተ ሰዎች የአካይያ በኩራት እንደ ሆኑ ቅዱሳንንም ለማገልገል ራሳቸውን እንደ ሰጡ ታውቃላችሁ፤
[16] እንደ እነርሱ ላሉትና አብሮ ለሚሠራ ለሚደክምም ሁሉ እናንተም እንድትገዙ እለምናችኋለሁ።
[17] በእስጢፋኖስና በፈርዶናጥስ በአካይቆስም መምጣት ደስ ይለኛል፥ እናንተ ስለሌላችሁ የጎደለኝን ፈጽመዋልና፤ መንፈሴንና መንፈሳችሁን አሳርፈዋልና።
[18] እንግዲህ እንደነዚህ ያሉትን እወቁአቸው።
[19] የእስያ አብያተ ክርስቲያናት ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። አቂላና ጵርስቅላ በቤታቸው ካለች ቤተ ክርስቲያን ጋር በጌታ እጅግ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።
[20] ወንድሞች ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። በተቀደሰ አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ።
[21] እኔ ጳውሎስ ይህን ሰላምታ በገዛ እጄ ጽፌአለሁ።
[22] ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን። ጌታችን ሆይ፥ ና።
[23] የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።
[24] ፍቅሬ በክርስቶስ ኢየሱስ ከሁላችሁ ጋር ነው። አሜን።