[1] እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ።
[2] ወንድሞች ሆይ፥ በሁሉ ስለምታስቡኝና አሳልፌ እንደ ሰጠኋችሁ ወግን ፈጽማችሁ ስለ ያዛችሁ አመሰግናችኋለሁ።
[3] ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፥ የሴትም ራስ ወንድ፥ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ልታውቁ እወዳለሁ።
[4] ራሱን ተከናንቦ የሚጸልይ ወይም ትንቢት የሚናገር ወንድ ሁሉ ራሱን ያዋርዳል።
[5] ራስዋን ሳትሸፍን ግን የምትጸልይ ወይም ትንቢት የምትናገር ሴት ሁሉ ራስዋን ታዋርዳለች፤ እንደ ተላጨች ያህል አንድ ነውና።
[6] ሴትም ራስዋን ባትሸፍን ጠጉርዋን ደግሞ ትቆረጥ፤ ለሴት ግን ጠጉርዋን መቆረጥ ወይም መላጨት የሚያሳፍር ከሆነ ራስዋን ትሸፍን።
[7] ወንድ የእግዚአብሔር ምሳሌና ክብር ስለ ሆነ ራሱን መከናነብ አይገባውም፤ ሴት ግን የወንድ ክብር ናት።
[8] ሴት ከወንድ ናት እንጂ ወንድ ከሴት አይደለምና።
[9] ሴት ስለ ወንድ ተፈጠረች እንጂ ወንድ ስለ ሴት አልተፈጠረምና።
[10] ስለዚህ ሴት ከመላእክት የተነሣ በራስዋ ሥልጣን ሊኖራት ይገባል።
[11] ነገር ግን በጌታ ዘንድ ሴት ያለ ወንድ ወንድም ያለ ሴት አይሆንም።
[12] ሴት ከወንድ እንደ ሆነች እንዲሁ ወንድ ደግሞ በሴት ነውና፤ ሁሉም ከእግዚአብሔር ነው።
[13] በእናንተ በራሳችሁ መካከል ፍረዱ፤ ሴት ራስዋን ሳትሸፍን ወደ እግዚአብሔር ልትጸልይ ይገባታልን?
[14] -
[15] ወንድ ጠጉሩን ቢያስረዝም ነውር እንዲሆንበት፥ ሴት ግን ጠጉርዋን ብታስረዝም ክብር እንዲሆንላት ተፈጥሮ እንኳ አያስተምራችሁምን? ጠጉርዋ መጎናጸፊያ ሊሆን ተሰጥቶአታልና።
[16] ዳሩ ግን ማንም ሊከራከር ቢፈቅድ፥ እኛ ወይም የእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት እንዲህ ያለ ልማድ የለንም።
[17] ነገር ግን በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለሚከፋ እንጂ ለሚሻል ስላልሆነ ይህን ትእዛዝ ስሰጥ የማመሰግናችሁ አይደለም።
[18] በመጀመሪያ ወደ ማኅበር ስትሰበሰቡ በመካከላችሁ መለያየት እንዳለ እሰማለሁና፥ በአንድ በኩልም አምናለሁ።
[19] በእናንተ ዘንድ የተፈተኑት እንዲገለጡ በመካከላችሁ ወገኖች ደግሞ ሊሆኑ ግድ ነውና።
[20] እንግዲህ አብራችሁ ስትሰበሰቡ የምትበሉት የጌታ እራት አይደለም፤
[21] በመብላት ጊዜ እያንዳንዱ የራሱን እራት ይበላልና፥ አንዱም ይራባል አንዱ ግን ይሰክራል።
[22] የምትበሉባቸውና የምትጠጡባቸው ቤቶች የላችሁምን? ወይስ የእግዚአብሔርን ማኅበር ትንቃላችሁን አንዳችም የሌላቸውን ታሳፍራላችሁን? ምን ልበላችሁ? በዚህ ነገር ላመስግናችሁን? አላመሰግናችሁም።
[23] ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና፤
[24] ጌታ ኢየሱስ አልፎ በተሰጠበት በዚያች ሌሊት እንጀራን አንሥቶ አመሰገነ፥ ቆርሶም። እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ።
[25] እንደዚሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን ደግሞ አንሥቶ። ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው፤ በጠጣችሁት ጊዜ ሁሉ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ።
[26] ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፥ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና።
[27] ስለዚህ ሳይገባው ይህን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት።
[28] ሰው ግን ራሱን ይፈትን፥ እንዲሁም ከእንጀራው ይብላ ከጽዋውም ይጠጣ፤
[29] ሳይገባው የሚበላና የሚጠጣ የጌታን ሥጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላልና፥ ይጠጣልምና።
[30] ስለዚህ በእናንተ ዘንድ የደከሙና የታመሙ ብዙዎች አሉ አያሌዎችም አንቀላፍተዋል።
[31] ራሳችንን ብንመረምር ግን ባልተፈረደብንም ነበር፤
[32] ነገር ግን በተፈረደብን ጊዜ ከዓለም ጋር እንዳንኮነን በጌታ እንገሠጻለን።
[33] ስለዚህ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ ለመብላት በተሰበሰባችሁ ጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ።
[34] ማንም የራበው ቢኖር ለፍርድ እንዳትሰበሰቡ በቤቱ ይብላ። የቀረውንም ነገር በመጣሁ ጊዜ እደነግጋለሁ።