Skip to content
Opens in a new window

[1] በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ።

[2] ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ።

[3] ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም።

[4] ፍቅር ይታገሣል፥ ቸርነትንም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፥ አይታበይም፤

[5] የማይገባውን አያደርግም፥ የራሱንም አይፈልግም፥ አይበሳጭም፥ በደልን አይቆጥርም፤

[6] ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ ዓመፃ ደስ አይለውም፤

[7] ሁሉን ይታገሣል፥ ሁሉን ያምናል፥ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፥ በሁሉ ይጸናል።

[8] ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም፤ ትንቢት ቢሆን ግን ይሻራል፤ ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ፤ እውቀትም ቢሆን ይሻራል።

[9] ከእውቀት ከፍለን እናውቃለንና፥ ከትንቢትም ከፍለን እንናገራለንና፤

[10] ፍጹም የሆነ ሲመጣ ግን ተከፍሎ የነበረው ይሻራል።

[11] ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ እናገር ነበር፥ እንደ ልጅም አስብ ነበር፥ እንደ ልጅም እቈጥር ነበር፤ ጎልማሳ ሆኜ ግን የልጅነትን ጠባይ ሽሬአለሁ።

[12] ዛሬስ በመስተዋት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን፤ ዛሬስ ከእውቀት ከፍዬ አውቃለሁ በዚያን ጊዜ ግን እኔ ደግሞ እንደ ታወቅሁ አውቃለሁ።

[13] እንዲህም ከሆነ፥ እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው።

ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1 — Chapters