Skip to content
Opens in a new window

[1] ከዚህም በኋላ በአራቱ በምድር ማዕዘን ቆመው አራት መላእክት አየሁ፥ እነርሱም ነፋስ በምድር ቢሆን ወይም በባሕር ወይም በማንም ዛፍ እንዳይነፍስ አራቱን የምድር ነፋሳት ያዙ።

[2] የሕያው አምላክ ማኅተም ያለውም ሌላ መልአክ ከፀሐይ መውጫ ሲወጣ አየሁ፥ ምድርንና ባሕርንም ሊጐዱ ለተሰጣቸው ለአራቱ መላእክት በታላቅ ድምፅ እየጮኸ።

[3] የአምላካችንን ባሪያዎች ግምባራቸውን እስክናትማቸው ድረስ ምድርን ቢሆን ወይም ባሕርን ወይም ዛፎችን አትጕዱ አላቸው።

[4] የታተሙትንም ቍጥር ሰማሁ፤ ከእስራኤል ልጆች ነገድ ሁሉ የታተሙት መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ።

[5] ከይሁዳ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ፥ ከሮቤል ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከጋድ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥

[6] ከአሴር ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከንፍታሌም ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥

[7] ከምናሴ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከስምዖን ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከሌዊ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከይሳኮር ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥

[8] ከዛብሎን ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከዮሴፍ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከብንያም ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ።

[9] ከዚህ በኋላ አየሁ፥ እነሆም፥ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤

[10] በታላቅም ድምፅ እየጮሁ። በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው አሉ።

[11] መላእክቱም ሁሉ በዙፋኑና በሽማግሌዎቹ በአራቱም እንስሶቹ ዙሪያ ቆመው ነበር፤ በዙፋኑም ፊት በግምባራቸው ተደፉ፥ ለእግዚአብሔርም እየሰገዱ።

[12] አሜን፥ በረከትና ክብር ጥበብም ምስጋናም ውዳሴም ኃይልም ብርታትም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን፤ አሜን አሉ።

[13] ከሽማግሌዎቹም አንዱ ተመልሶ። እነዚህ ነጩን ልብስ የለበሱ እነማን ናቸው? ከወዴትስ መጡ? አለኝ።

[14] እኔም። ጌታ ሆይ፥ አንተ ታውቃለህ አልሁት። አለኝም። እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፥ ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም አነጹ።

[15] ስለዚህ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት አሉ፥ ሌሊትና ቀንም በመቅደሱ ያመልኩታል፥ በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው በእነርሱ ላይ ያድርባቸዋል።

[16] ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም፥ ከእንግዲህም ወዲህ አይጠሙም፥ ፀሐይም ትኵሳትም ሁሉ ከቶ አይወርድባቸውም፤

[17] በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና፥ ወደ ሕይወትም ውኃ ምንጭ ይመራቸዋልና፤ እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል።

የዮሐንስ ራእይ። የዮሐንስ ራእይ — Chapters