[1] በሰርዴስም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ። ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስትና ሰባቱ ከዋክብት ያሉት እንዲህ ይላል። ሥራህን አውቃለሁ ሕያው እንደ መሆንህ ስም አለህ ሞተህማል።
[2] ሥራህን በአምላኬ ፊት ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትምና የነቃህ ሁን፥ ሊሞቱም ያላቸውን የቀሩትን ነገሮች አጽና።
[3] እንግዲህ እንዴት እንደ ተቀበልህና እንደ ሰማህ አስብ፥ ጠብቀውም ንስሐም ግባ። እንግዲያስ ባትነቃ እንደ ሌባ እመጣብሃለሁ በማናቸውም ሰዓት እንድመጣብህ ከቶ አታውቅም።
[4] ነገር ግን ልብሳቸውን ያላረከሱ በሰርዴስ ጥቂት ሰዎች ከአንተ ጋር አሉ፥ የተገባቸውም ስለ ሆኑ ነጭ ልብስ ለብሰው ከእኔ ጋር ይሄዳሉ።
[5] ድል የነሣው እንዲሁ በነጭ ልብስ ይጐናጸፋል፥ ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም፥ በአባቴና በመላእክቱም ፊት ለስሙ እመሰክርለታለሁ።
[6] መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።
[7] በፊልድልፍያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ። የዳዊት መክፈቻ ያለው፤ የሚከፍት፥ የሚዘጋም የሌለ፤ የሚዘጋ፥ የሚከፍትም የሌለ፤ ቅዱስና እውነተኛ የሆነው እርሱ እንዲህ ይላል።
[8] ሥራህን አውቃለሁ፤ እነሆ፥ በአንተ ፊት የተከፈተ በር ሰጥቼአለሁ ማንምም ሊዘጋው አይችልም፤ ኃይልህ ምንም ትንሽ ቢሆን ቃሌን ጠብቀሃልና፥ ስሜንም አልካድህምና።
[9] እነሆ፥ አይሁድ ሳይሆኑ። አይሁድ ነን ከሚሉ ነገር ግን ከሚዋሹ ከሰይጣን ማኅበር አንዳንዶችን እሰጥሃለሁ እነሆ፥ መጥተው በእግሮችህ ፊት ይሰግዱ ዘንድ እኔም እንደ ወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ።
[10] የትዕግሥቴን ቃል ስለ ጠበቅህ እኔ ደግሞ በምድር የሚኖሩትን ይፈትናቸው ዘንድ በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው ከፈተናው ሰዓት እጠብቅሃለሁ።
[11] እነሆ፥ ቶሎ ብዬ እመጣለሁ፤ ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጽንተህ ያዝ።
[12] ድል የነሣው በአምላኬ መቅደስ ዓምድ እንዲሆን አደርገዋለሁ፥ ወደ ፊትም ከዚያ ከቶ አይወጣም፤ የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም፥ ማለት ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን አዲሲቱን ኢየሩሳሌምን፥ አዲሱንም ስሜን በእርሱ ላይ እጽፋለሁ።
[13] መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።
[14] በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ። አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል።
[15] በራድ ወይም ትኩስ እንዳይደለህ ሥራህን አውቃለሁ። በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም በሆነ ነበር።
[16] እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው።
[17] ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም የምትል ስለ ሆንህ፥ ጐስቋላና ምስኪንም ድሀም ዕውርም የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ፥
[18] ባለ ጠጋ እንድትሆን በእሳት የነጠረውን ወርቅ፥ ተጐናጽፈህም የራቁትነትህ ኃፍረት እንዳይገለጥ ነጭ ልብስን፥ እንድታይም ዓይኖችህን የምትኳለውን ኵል ከእኔ ትገዛ ዘንድ እመክርሃለሁ።
[19] እኔ የምወዳቸውን ሁሉ እገሥጻቸዋለሁ እቀጣቸውማለሁ፤ እንግዲህ ቅና ንስሐም ግባ።
[20] እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል።
[21] እኔ ደግሞ ድል እንደ ነሣሁ ከአባቴም ጋር በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጥሁ፥ ድል ለነሣው ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ ዘንድ እሰጠዋለሁ።
[22] መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።