[1] አንድም አውሬ ከባሕር ሲወጣ አየሁ፤ አሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ነበሩት፥ በቀንዶቹም ላይ አሥር ዘውዶች በራሶቹም ላይ የስድብ ስም ነበረ።
[2] ያየሁትም አውሬ ነብር ይመስል ነበር፥ እግሮቹም እንደ ድብ እግሮች፥ አፉም እንደ አንበሳ አፍ ነበሩ። ዘንዶውም ኃይሉንና ዙፋኑን ትልቅም ሥልጣን ሰጠው።
[3] ከራሶቹም ለሞት እንደ ታረደ ሆኖ አንዱን አየሁ፥ ለሞቱ የሆነውም ቍስል ተፈወሰ። ምድርም ሁሉ አውሬውን እየተከተለ ተደነቀ፥
[4] ለዘንዶውም ሰገዱለት፥ ለአውሬው ሥልጣንን ሰጥቶታልና፤ ለአውሬውም። አውሬውን ማን ይመስለዋል፥ እርሱንስ ሊዋጋ ማን ይችላል? እያሉ ሰገዱለት።
[5] ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው፥ በአርባ ሁለት ወርም እንዲሠራ ሥልጣን ተሰጠው።
[6] እግዚአብሔርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ።
[7] ቅዱሳንንም ይዋጋ ዘንድ ድልም ያደርጋቸው ዘንድ ተሰጠው፥ በነገድና በወገንም በቋንቋም በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው።
[8] ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በታረደው በግ ሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ ሁሉ ይሰግዱለታል።
[9] ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ።
[10] ይማረክ ዘንድ ያለው ማንም ቢኖር ወደ ምርኮነት ይሄዳል፤ በሰይፍ የሚገድል ማንም ቢኖር ራሱ በሰይፍ እንዲገደል ይገባዋል። የቅዱሳን ትዕግሥትና እምነት በዚህ ነው።
[11] ሌላም አውሬ ከምድር ሲወጣ አየሁ፥ የበግ ቀንዶችን የሚመስሉ ሁለት ቀንዶችም ነበሩት እንደ ዘንዶም ይናገር ነበር።
[12] በፊተኛውም አውሬ ሥልጣን በእርሱ ፊት ሁሉን ያደርጋል። ለሞቱ የሆነውም ቍስል ተፈወሰለት ለፊተኛው አውሬ ምድርና በእርሱ የሚኖሩት እንዲሰግዱለት ያደርጋል።
[13] እሳትንም እንኳ ከሰማይ ወደ ምድር በሰው ፊት እስኪያወርድ ድረስ ታላላቆችን ምልክቶች ያደርጋል።
[14] በአውሬውም ፊት ያደርግ ዘንድ ከተሰጡት ምልክቶች የተነሣ በምድር የሚኖሩትን ያስታል፤ የሰይፍም ቍስል ለነበረውና በሕይወት ለኖረው ለአውሬው ምስልን እንዲያደርጉ በምድር የሚኖሩትን ይናገራል።
[15] የአውሬው ምስል ሊናገር እንኳ ለአውሬውም ምስል የማይሰግዱለትን ሁሉ ሊያስገድላቸው፥ ለአውሬው ምስል ትንፋሽ እንዲሰጠው ተሰጠው።
[16] ታናናሾችና ታላላቆችም ባለ ጠጋዎችና ድሆችም ጌታዎችና ባሪያዎችም ሁሉ በቀኝ እጃቸው ወይም በግምባራቸው ምልክትን እንዲቀበሉ፥
[17] የአውሬውም ስም ወይም የስሙ ቍጥር ያለው ምልክት የሌለበት ማንም ሊገዛ ወይም ሊሸጥ እንዳይችል ያደርጋል። ጥበብ በዚህ አለ።
[18] አእምሮ ያለው የአውሬውን ቍጥር ይቍጠረው፤ ቍጥሩ የሰው ቍጥር ነውና፥ ቍጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው።