Skip to content
Opens in a new window

[1] ወደ ኢየሩሳሌምም ቀርበው ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ፥ ያንጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከ፥

[2] እንዲህም አላቸው። በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከእርስዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ።

[3] ማንም አንዳች ቢላችሁ። ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል።

[4] -

[5] ለጽዮን ልጅ። እነሆ፥ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሉአት ተብሎ በነቢይ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ።

[6] ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፥

[7] አህያይቱንና ውርንጫዋንም አመጡለት፥ ልብሳቸውንም በእነርሱ ላይ ጫኑ፥ ተቀመጠባቸውም።

[8] ከሕዝቡም እጅግ ብዙዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፥ ሌሎችም ከዛፍ ጫፍ ጫፉን እየቈረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር።

[9] የሚቀድሙትም ሕዝብ የሚከተሉትም። ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር።

[10] ወደ ኢየሩሳሌምም በገባ ጊዜ መላው ከተማ። ይህ ማን ነው? ብሎ ተናወጠ።

[11] ሕዝቡም። ይህ ከገሊላ ናዝሬት የመጣ ነቢዩ ኢየሱስ ነው አሉ።

[12] ኢየሱስም ወደ መቅደስ ገባና በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አወጣ፥ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠና።

[13] ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎአል፥ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት አላቸው።

[14] በመቅደስም ዕውሮችና አንካሶች ወደ እርሱ ቀረቡና ፈወሳቸው።

[15] ነገር ግን የካህናት አለቆችና ጻፎች ያደረገውን ድንቃ ድንቅ በመቅደስም። ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፥ ተቈጥተው።

[16] እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን? አሉት። ኢየሱስም። እሰማለሁ፤ ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን? አላቸው።

[17] ትቶአቸውም ከከተማ ወደ ቢታንያ ወጣ በዚያም አደረ።

[18] በማለዳም ወደ ከተማ ሲመለስ ተራበ።

[19] በመንገድም አጠገብ በለስ አይቶ ወደ እርስዋ መጣ፤ ከቅጠልም ብቻ በቀር ምንም አላገኘባትምና። ለዘላለሙ ፍሬ አይገኝብሽ አላት። በለሲቱም ያንጊዜውን ደረቀች።

[20] ደቀ መዛሙርቱም ይህን አይተው። በለሲቱ ያንጊዜውን እንዴት ደረቀች? ብለው ተደነቁ።

[21] ኢየሱስም መልሶ። እውነት እላችኋለሁ፥ እምነት ቢኖራችሁ ባትጠራጠሩም፥ በበለሲቱ እንደ ሆነባት ብቻ አታደርጉም፤ ነገር ግን ይህን ተራራ እንኳ። ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ብትሉት ይሆናል፤

[22] አምናችሁም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ አላቸው።

[23] ወደ መቅደስም ገብቶ ሲያስተምር የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሎች ወደ እርሱ ቀረቡና። በምን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ? አሉት።

[24] ኢየሱስም መልሶ። እኔ ደግሞ አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፤ እናንተም ያችን ብትነግሩኝ እኔ ደግሞ እነዚህን በምን ሥልጣን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ፤

[25] የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይን ወይስ ከሰው? አላቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ። ከሰማይ ብንል። እንኪያስ ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤

[26] ከሰው ግን ብንል፥ ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ያዩታልና ሕዝቡን እንፈራለን አሉ።

[27] ለኢየሱስም መልሰው። አናውቅም አሉት። እርሱም ደግሞ። እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም አላቸው።

[28] ነገር ግን ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤ ወደ አንደኛው ቀርቦ። ልጄ ሆይ፥ ዛሬ ሂድና በወይኔ አትክልት ሥራ አለው።

[29] እርሱም መልሶ። አልወድም አለ፤ ኋላ ግን ተጸጸተና ሄደ።

[30] ወደ ሁለተኛውም ቀርቦ እንዲሁ አለው እርሱም መልሶ። እሺ ጌታዬ አለ፤ ነገር ግን አልሄደም።

[31] ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ ያደረገ ማን ነው? ፊተኛው አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው። እውነት እላችኋለሁ፥ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል።

[32] ዮሐንስ በጽድቅ መንገድ መጥቶላችሁ ነበርና፥ አላመናችሁበትም፤ ቀራጮችና ጋለሞቶች ግን አመኑበት፤ እናንተም ይህን አይታችሁ ታምኑበት ዘንድ በኋላ ንስሐ አልገባችሁም።

[33] ሌላ ምሳሌ ስሙ። የወይን አትክልት የተከለ ባለቤት ሰው ነበረ፤ ቅጥርም ቀጠረለት፥ መጥመቂያም ማሰለት፥ ግንብም ሠራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ።

[34] የሚያፈራበትም ጊዜ ሲቀርብ፥ ፍሬውን ሊቀበሉ ባሮቹን ወደ ገበሬዎች ላከ።

[35] ገበሬዎቹም ባሮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት አንዱንም ገደሉት ሌላውንም ወገሩት።

[36] ደግሞ ከፊተኞች የሚበዙ ሌሎች ባሮችን ላከ፥ እንዲሁም አደረጉባቸው።

[37] በኋላ ግን። ልጄንስ ያፍሩታል ብሎ ልጁን ላከባቸው።

[38] ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩ ጊዜ እርስ በርሳቸው። ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፥ እንግደለውና ርስቱን እናግኝ ተባባሉ።

[39] ይዘውም ከወይኑ አትክልት አወጡና ገደሉት።

[40] እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ በሚመጣ ጊዜ በእነዚህ ገበሬዎች ምን ያደርግባቸዋል?

[41] እነርሱም። ክፉዎችን በክፉ ያጠፋቸዋል፥ የወይኑንም አትክልት ፍሬውን በየጊዜው ለሚያስረክቡ ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጠዋል አሉት።

[42] ኢየሱስ እንዲህ አላቸው። ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፥ ለዓይኖቻችንም ድንቅ ነው የሚለውን ከቶ በመጽሐፍ አላነበባችሁምን?

[43] ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች።

[44] በዚህም ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይቀጠቀጣል፤ ድንጋዩ ግን የሚወድቅበትን ሁሉ ይፈጨዋል።

[45] የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ምሳሌዎቹን ሰምተው ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አስተዋሉ፤

[46] ሊይዙትም ሲፈልጉት ሳሉ ሕዝቡ እንደ ነቢይ ስላዩት ፈሩአቸው።

የማቴዎስ ወንጌል። — Chapters