Skip to content
Opens in a new window

[1] የዳዊት ልጅ የአብርሃም ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ትውልድ መጽሐፍ።

[2] አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፤ ይስሐቅም ያዕቆብን ወለደ፤ ያዕቆብም ይሁዳንና ወንድሞቹን ወለደ፤

[3] ይሁዳም ከትዕማር ፋሬስንና ዛራን ወለደ፤ ፋሬስም ኤስሮምን ወለደ፤

[4] ኤስሮምም አራምን ወለደ፤ አራምም አሚናዳብን ወለደ፤ አሚናዳብም ነአሶንን ወለደ፤ ነአሶንም ሰልሞንን ወለደ፤

[5] ሰልሞንም ከራኬብ ቦኤዝን ወለደ፤ ቦኤዝም ከሩት ኢዮቤድን ወለደ፤ ኢዮቤድም እሴይን ወለደ፤

[6] እሴይም ንጉሥ ዳዊትን ወለደ።

[7] ሰሎሞንም ሮብዓምን ወለደ፤ ሮብዓምም አቢያን ወለደ፤ አቢያም አሣፍን ወለደ፤

[8] አሣፍም ኢዮሣፍጥን ወለደ፤ ኢዮሣፍጥም ኢዮራምን ወለደ፤ ኢዮራምም ዖዝያንን ወለደ፤

[9] ዖዝያንም ኢዮአታምን ወለደ፤ ኢዮአታምም አካዝን ወለደ፤

[10] አካዝም ሕዝቅያስን ወለደ፤ ሕዝቅያስም ምናሴን ወለደ፤ ምናሴም አሞፅን ወለደ፤

[11] አሞፅም ኢዮስያስን ወለደ፤ ኢዮስያስም በባቢሎን ምርኮ ጊዜ ኢኮንያንንና ወንድሞቹን ወለደ።

[12] ከባቢሎንም ምርኮ በኋላ ኢኮንያን ሰላትያልን ወለደ፤ ሰላትያልም ዘሩባቤልን ወለደ፤

[13] ዘሩባቤልም አብዩድን ወለደ፤ አብዩድም ኤልያቄምን ወለደ፤ ኤልያቄምም አዛርን ወለደ፤

[14] አዛርም ሳዶቅን ወለደ፤ ሳዶቅም አኪምን ወለደ፤ አኪምም ኤልዩድን ወለደ፤

[15] ኤልዩድም አልዓዛርን ወለደ፤ አልዓዛርም ማታንን ወለደ፤ ማታንም ያዕቆብን ወለደ፤

[16] ያዕቆብም ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን የወለደች የማርያምን እጮኛ ዮሴፍን ወለደ።

[17] እንግዲህ ትውልድ ሁሉ ከአብርሃም እስከ ዳዊት አሥራ አራት ትውልድ፥ ከዳዊትም እስከ ባቢሎን ምርኮ አሥራ አራት ትውልድ፥ ከባቢሎንም ምርኮ እስከ ክርስቶስ አሥራ አራት ትውልድ ነው።

[18] የኢየሱስ ክርስቶስም ልደት እንዲህ ነበረ። እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች።

[19] እጮኛዋ ዮሴፍም ጻድቅ ሆኖ ሊገልጣት ስላልወደደ በስውር ሊተዋት አሰበ።

[20] እርሱ ግን ይህን ሲያስብ፥ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው፥ እንዲህም አለ። የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፥ ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ።

[21] ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።

[22] በነቢይ ከጌታ ዘንድ።

[23] እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፥ ትርጓሜውም። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው።

[24] ዮሴፍም ከእንቅልፉ ነቅቶ የጌታ መልአክ እንዳዘዘው አደረገ፤ እጮኛውንም ወሰደ፤

[25] የበኩር ልጅዋንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም፤ ስሙንም ኢየሱስ አለው።

የማቴዎስ ወንጌል። — Chapters