[1] መንግሥተ ሰማያት ለወይኑ አትክልት ሠራተኞችን ሊቀጥር ማልዶ የወጣ ባለቤት ሰውን ትመስላለችና።
[2] ሠራተኞችንም በቀን አንድ ዲናር ተስማምቶ ወደ ወይኑ አትክልት ሰደዳቸው።
[3] በሦስት ሰዓትም ወጥቶ ሥራ የፈቱ ሌሎችን በአደባባይ ቆመው አየ፥
[4] እነዚያንም። እናንተ ደግሞ ወደ ወይኔ አትክልት ሂዱ የሚገባውንም እሰጣችኋለሁ አላቸው። እነርሱም ሄዱ።
[5] ደግሞም በስድስትና በዘጠኝ ሰዓት ወጥቶ እንዲሁ አደረገ።
[6] በአሥራ አንደኛውም ሰዓት ወጥቶ ሌሎችን ቆመው አገኘና። ሥራ ፈትታችሁ ቀኑን ሁሉ በዚህ ስለ ምን ትቆማላችሁ? አላቸው።
[7] የሚቀጥረን ስለ አጣን ነው አሉት። እርሱም። እናንተ ደግሞ ወደ ወይኔ አትክልት ሂዱ የሚገባውንም ትቀበላላችሁ አላቸው።
[8] በመሸም ጊዜ የወይኑ አትክልት ጌታ አዛዡን። ሠራተኞችን ጥራና ከኋለኞች ጀምረህ እስከ ፊተኞች ድረስ ደመወዝ ስጣቸው አለው።
[9] በአሥራ አንደኛው ሰዓትም የገቡ መጥተው እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ።
[10] ፊተኞችም በመጡ ጊዜ አብዝተው የሚቀበሉ መስሎአቸው ነበር፤ እነርሱም ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ።
[11] -
[12] ተቀብለውም። እነዚህ ኋለኞች አንድ ሰዓት ሠሩ፥ የቀኑንም ድካምና ትኩሳት ከተሸከምን ከእኛ ጋር አስተካከልሃቸው ብለው በባለቤቱ ላይ አንጐራጐሩ።
[13] እርሱ ግን መልሶ ከእነርሱ ለአንዱ እንዲህ አለው። ወዳጄ ሆይ፥ አልበደልሁህም በአንድ ዲናር አልተስማማኸኝምን?
[14] ድርሻህን ውሰድና ሂድ፤ እኔ ለዚህ ለኋለኛው እንደ አንተ ልሰጠው እወዳለሁ፤ በገንዘቤ የወደድሁትን አደርግ ዘንድ መብት የለኝምን?
[15] ወይስ እኔ መልካም ስለ ሆንሁ ዓይንህ ምቀኛ ናትን?
[16] እንዲሁ ኋለኞች ፊተኞች፥ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ፤ የተጠሩ ብዙዎች፥ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና።
[17] ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ሊወጣ ሳለ፥ በመንገድ አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ብቻቸውን ወደ እርሱ አቅርቦ።
[18] እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፥ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች ይሰጣል፤ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፥
[19] ሊዘባበቱበትም ሊገርፉትም ሊሰቅሉትም ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል አላቸው።
[20] በዚያን ጊዜ የዘብዴዎስ ልጆች እናት ከልጆችዋ ጋር እየሰገደችና አንድ ነገር እየለመነች ወደ እርሱ ቀረበች።
[21] እርሱም። ምን ትፈልጊያለሽ? አላት። እርስዋም። እነዚህ ሁለቱ ልጆቼ አንዱ በቀኝህ አንዱም በግራህ በመንግሥትህ እንዲቀመጡ እዘዝ አለችው።
[22] ኢየሱስ ግን መልሶ። የምትለምኑትን አታውቁም። እኔ ልጠጣው ያለውን ጽዋ ልትጠጡ እኔም የምጠመቀውን ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁን? አለ። እንችላለን አሉት።
[23] እርሱም። ጽዋዬንስ ትጠጣላችሁ፤ በቀኝና በግራ መቀመጥ ግን ከአባቴ ዘንድ ለተዘጋጀላቸው ነው እንጂ እኔ የምሰጥ አይደለሁም አላቸው።
[24] አሥሩም ሰምተው በሁለቱ ወንድማማች ተቈጡ።
[25] ኢየሱስ ግን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው። የአሕዛብ አለቆች እንዲገዙአቸው ታላላቆቹም በላያቸው እንዲሠለጥኑ ታውቃላችሁ።
[26] በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፥
[27] ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን፤
[28] እንዲሁም የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።
[29] ከኢያሪኮም ሲወጡ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት።
[30] እነሆም፥ ሁለት ዕውሮች በመንገድ ዳር ተቀምጠው፥ ኢየሱስ እንዲያልፍ በሰሙ ጊዜ። ጌታ ሆይ፥ የዳዊት ልጅ፥ ማረን ብለው ጮኹ።
[31] ሕዝቡም ዝም እንዲሉ ገሠጹአቸው፤ እነርሱ ግን። ጌታ ሆይ፥ የዳዊት ልጅ፥ ማረን እያሉ አብዝተው ጮኹ።
[32] ኢየሱስም ቆሞ ጠራቸውና። ምን ላደርግላችሁ ትወዳላችሁ? አለ።
[33] ጌታ ሆይ፥ ዓይኖቻችን ይከፈቱ ዘንድ አሉት።
[34] ኢየሱስም አዘነላቸውና ዓይኖቻቸውን ዳሰሰ፥ ወዲያውም አዩና ተከተሉት።