Skip to content
Opens in a new window

[1] ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና።

[2] በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለንና፥

[3] ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ እንናፍቃለንና ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም።

[4] በእውነትም የሚሞተው በሕይወት ይዋጥ ዘንድ ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ የማንወድ ስለ ሆነ፥ በድንኳኑ ያለን እኛ ከብዶን እንቃትታለን።

[5] ነገር ግን ለዚሁ የሠራን እግዚአብሔር ነው እርሱም የመንፈሱን መያዣ ሰጠን።

[6] -

[7] እንግዲህ ሁልጊዜ ታምነን፥ በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስምና በሥጋ ስናድር ከጌታ ተለይተን በስደት እንዳለን የምናውቅ ከሆንን፥

[8] ታምነናል ይልቁንም ከሥጋ ተለይተን በስደት መኖር በጌታም ዘንድ ማደር ደስ ይለናል።

[9] ስለዚህ ደግሞ ብናድር ወይም ተለይተን ብንሆን እርሱን ደስ የምናሰኝ ልንሆን እንቀናለን።

[10] መልካም ቢሆን ወይም ክፉ እንዳደረገ፥ እያንዳንዱ በሥጋው የተሠራውን በብድራት ይቀበል ዘንድ ሁላችን በክርስቶስ በፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናልና።

[11] እንግዲህ የጌታን ፍርሃት አውቀን ሰዎችን እናስረዳለን ለእግዚአብሔር ግን የተገለጥን ነን፤ በሕሊናችሁም ደግሞ የተገለጥን እንደ ሆንን ተስፋ አደርጋለሁ።

[12] በመልክ እንጂ በልብ ለማይመኩ የምትመልሱላቸው መልስ እንዲኖራችሁ፥ በእኛ ልትመኩ ምክንያት እንሰጣችኋለን እንጂ ራሳችንን ደግሞ ለእናንተ የምናመሰግን አይደለንም።

[13] እብዶች ብንሆን፥ ለእግዚአብሔር ነው፤ ባለ አእምሮዎች ብንሆን፥ ለእናንተ ነው።

[14] ይህን ስለቆረጥን የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፤ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ፤

[15] በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ።

[16] ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም።

[17] ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል።

[18] ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው፤

[19] እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ።

[20] እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን።

[21] እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው።

ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2 — Chapters