[1] ነገር ግን ዳግመኛ በኀዘን ወደ እናንተ እንዳልመጣ ስለ እኔ ቆረጥሁ።
[2] እኔስ ባሳዝናችሁ፥ እንግዲያስ በእኔ ምክንያት ከሚያዝን በቀር ደስ የሚያሰኘኝ ማን ነው?
[3] ደስ ሊያሰኙኝ ከሚገባቸውም በመምጣቴ ኀዘን እንዳይሆንብኝ ይህንኑ ጻፍሁላችሁ፥ ደስታዬ የሁላችሁ ደስታ ነው ብዬ በሁላችሁ ታምኜአለሁና።
[4] በብዙ መከራና ከልብ ጭንቀት በብዙም እንባ ጽፌላችሁ ነበርና፤ ይህም እናንተን አብዝቼ የምወድበትን ፍቅር እንድታውቁ እንጂ እንዳሳዝናችሁ አይደለም።
[5] ነገር ግን ማንም አሳዝኖ ቢሆን፥ እንዳልከብድባችሁ፥ በክፍል ሁላችሁን እንጂ እኔን ያሳዘነ አይደለም።
[6] እንደዚህ ላለ ሰው ይህ ከእናንተ የምትበዙት የቀጣችሁት ቅጣት ይበቃዋልና እንደዚህ ያለው ከልክ በሚበዛ ኀዘን እንዳይዋጥ፥
[7] ይልቅ ተመልሳችሁ ይቅር ማለትና ማጽናናት ይገባችኋል።
[8] ስለዚህ ከእርሱ ጋር ፍቅርን እንድታጸኑ እለምናችኋለሁ፤
[9] ስለዚህ ደግሞ ጽፌ ነበርና፤ በሁሉ የምትታዘዙ እንደ ሆናችሁ የእናንተን መፈተን አውቅ ዘንድ አሳቤ ነበር።
[10] እናንተ ግን ይቅር የምትሉትን እኔ ደግሞ ይቅር እለዋለሁ፤ እኔም ይቅር ካልሁ፥ ይቅር ያልሁትን ስለ እናንተ በክርስቶስ ፊት ይቅር ብዬአለሁ፥
[11] በሰይጣን እንዳንታለል፤ የእርሱን አሳብ አንስተውምና።
[12] ስለ ክርስቶስም ወንጌል ወደ ጢሮአዳ በመጣሁ ጊዜ፥ ለጌታ ሥራ በር ምንም ቢከፈትልኝ፥ ቲቶን ወንድሜን ስላላገኘሁት መንፈሴ ዕረፍት አልነበረውም፥
[13] ነገር ግን ከእነርሱ ተሰናብቼ ወደ መቄዶንያ ወጣሁ።
[14] ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን በእኛም በየስፍራው ሁሉ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ ለአምላክ ምስጋና ይሁን፤
[15] በሚድኑቱና በሚጠፉቱ ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ ነንና፤
[16] ለእነዚህ ለሞት የሚሆን የሞት ሽታ ለእነዚያም ለሕይወት የሚሆን የሕይወት ሽታ ነን። ለዚህም ነገር የሚበቃ ማን ነው?
[17] የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ ብዙዎቹ አይደለንምና፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን።