Skip to content
Opens in a new window

[1] ትምክህት የሚያስፈልግ ነው፤ አይጠቅምም ነገር ግን ከጌታ ወዳለው ራእይና መገለጥ እመጣለሁ።

[2] ሰውን በክርስቶስ አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም ወይም ከሥጋ ውጭ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ እንዲህ ያለው ሰው ከአሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ።

[3] እንዲህ ያለውንም ሰው አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ ወይም ያለ ሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤

[4] ወደ ገነት ተነጠቀ፥ ሰውም ሊናገር የማይገባውን የማይነገረውን ቃል ሰማ።

[5] እንደዚህ ስላለው እመካለሁ፥ ስለ ራሴ ግን ከድካሜ በቀር አልመካም።

[6] ልመካ ብወድስ ሞኝ አልሆንም፥ እውነትን እላለሁና፤ ነገር ግን ማንም ከሚያይ ከእኔም ከሚሰማ የምበልጥ አድርጎ እንዳይቆጥረኝ ትቼአለሁ።

[7] ስለዚህም በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ፥ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ፤ ይኸውም እንዳልታበይ ነው።

[8] ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ።

[9] እርሱም። ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ።

[10] ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና።

[11] በመመካቴ ሞኝ ሆኜአለሁ፤ እናንተ ግድ አላችሁኝ፤ እናንተ እኔን ልታመሰግኑ ይገባ ነበርና። እኔ ምንም ባልሆን እንኳ፥ ከዋነኞቹ ሐዋርያት በምንም አልጎድልምና።

[12] በእርግጥ የሐዋርያነት ምልክት በመካከላችሁ በምልክትና በድንቅ ነገር በተአምራትም በሁሉ ትዕግሥት ተደረገ።

[13] እኔ ራሴ ካልከበድሁባችሁ ከዚህ በቀር፥ ከሌላ ቤተ ክርስቲያን ያነሳችሁበት በምን እኮ ነው? ይህን በደሌን ይቅር በሉልኝ።

[14] እነሆ፥ ወደ እናንተ እመጣ ዘንድ ስዘጋጅ ይህ ሦስተኛዬ ነው፤ አልከብድባችሁምም፥ እናንተን እንጂ ያላችሁን አልፈልግምና። ወላጆች ለልጆች እንጂ ልጆች ለወላጆች ገንዘብ ሊያከማቹ አይገባቸውምና።

[15] እኔ ግን ስለ ነፍሳችሁ በብዙ ደስታ ገንዘቤን እከፍላለሁ፥ ራሴን እንኳ እከፍላለሁ። ከመጠን ይልቅ ብወዳችሁ በዚህ ልክ ፍቅራችሁ የሚያንስ ነውን?

[16] ይሁን እንጂ እኔ አልከበድሁባችሁም፤ ነገር ግን ሸንጋይ ሆኜ በተንኰል ያዝኋችሁ።

[17] ወደ እናንተ ከላክኋቸው በአንዱ ስንኳ አታለልኋችሁን?

[18] ቲቶን መከርሁት ከእርሱም ጋር ወንድሙን ላክሁት፤ ቲቶስ አታለላችሁን? በአንድ መንፈስ አልተመላለስንምን? በአንድ ፍለጋስ አልተመላለስንም?

[19] ለእናንተ ስለ ራሳችን እንድንመልስ ሁልጊዜ ይመስላችኋልን? በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን፤ ነገር ግን፥ ወዳጆች፥ እናንተን ልናንጻችሁ ሁሉን እንናገራለን።

[20] ስመጣ፥ እንደምወደው ሳትሆኑ አገኛችሁ ይሆናል እኔም እንደምትወዱት ሳልሆን ታገኙኝ ይሆናል ብዬ እፈራለሁና፤ ምናልባት ክርክር ቅንዓትም ቁጣም አድመኝነትም ሐሜትም ማሾክሾክም ኩራትም ሁከትም ይሆናሉ፤

[21] እንደ ገና ስመጣ በእናንተ ዘንድ አምላኬ እንዲያዋርደኝ፥ አስቀድመውም ኃጢአት ከሠሩትና ስላደረጉት ርኵሰትና ዝሙት መዳራትም ንስሐ ካልገቡት ወገን ስለ ብዙዎች ምናልባት አዝናለሁ ብዬ እፈራለሁ።

ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2 — Chapters