[1] ነገር ግን ሐሰተኟች ነቢያት ደግሞ በሕዝቡ መካከል ነበሩ፤ እንዲሁም በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኟች አስተማሪዎች ይኖራሉ፤ እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው፥ የሚፈጥን ጥፋትን በራሳቸው ላይ እየሳቡ፥ የሚያጠፋ ኑፋቄን አሾልከው ያስገባሉ።
[2] ብዙ ሰዎችም እነርሱን ስለ ዝሙታቸው ይከተሉአቸዋል፤ የጽድቅ መንገድንም ያሰድባሉ።
[3] ራሳቸውም በፈጠሩት ቃል ይከራከራሉ፤ በእርሱም ይሄዳሉ፤ ፍርዳቸውም ከጥንት ጀምሮ አይዘገይም፤ ጥፋታቸውም አያንቀላፋም።
[4] እግዚአብሔርስ መላእክቱን እንኳ ቢሆን በድለው አልራራላቸውም፤ የሚነድድ እሳት ወደ አለበት የደይን ሥቃይ ጣላቸው እንጂ፤ ሊኰነኑና በደይን ሥቃይም ሊኖሩ አሳልፎ ሰጣቸው።
[5] ለቀደሙት ሰዎችም አላዘነላቸውም፤ ነገር ግን እውነትን ይሰብክ ዘንድ እውነትን ከጠበቃት ከኖኅ ጋር ስምንት ነፍስን አተረፈ፤ በኀጢአተኟች ሰዎች ዓለም ላይም የጥፋትን ውኃ አመጣባቸው።
[6] የሰዶምና የገሞራ ሀገሮችንም አቃጠላቸው፤ ገለባበጣቸውም፤ እንዲህም ቀጣቸው፤ ለኋለኛው ዘመንም ለኃጥኣን ምሳሌ አደረጋቸው።
[7] የተገፋ ጻድቅ ሎጥን ግን በዝሙት ሥራቸው ከሚበድሉ ሰዎች ለይቶ አዳነው።
[8] ጻድቅ ሎጥም እያየና እየሰማ፥ አብሮአቸውም እየኖረ በክፉ ሥራቸው ከዕለት ወደ ዕለት ጻድቅት ነፍሱን ያስጨንቌት ነበር።
[9] እንግዲህ እነሆ፥ እግዚአብሔር ጻድቃንን ከመከራ እንደሚያድናቸው ያውቃል፤ ኃጥኣንን ግን ለፍርድ ቀን ለሥቃይ ይጠብቃቸዋል።
[10] ይልቁንም በርኩስ ምኟት የሥጋን ፍትወት እየተከተሉ የሚመላለሱትን፥ ፈጣሪያቸውንም የሚያቃልሉትንና በጌትነቱ ላይ የስድብ ቃል ሲናገሩ የማይፈሩትን፥ ደፋሮችንና ተሳዳቢዎችንም ለፍርድ ቀን ይጠብቃቸዋል።
[11] ነገር ግን መላእክት በኀይልና በብርታት ከእነርሱ ይልቅ ምንም ቢበልጡ በጌታ ፊት በእነርሱ ላይ የስድብን ፍርድ አያመጡም።
[12] እነዚህም ለጥፋት እንደ ተፈጠሩ፥ አእምሮ እንደሌላቸው እንስሳት ናቸው፤ ጥፋታቸውን ለማምጣት የማያውቁትን ይሳደባሉና፥ በጥፋታቸውም የዐመፅ ዋጋን ይቀበላሉ።
[13] በቀን መጠጥ ተድላ ማድረግን አሳምረው ይዘዋታል፤ እየሳሱም ይበላሉ፤ የማይጠግቡም ርኩሳን ናቸው፤ በፍቅራቸው ይሸነጋገላሉ፤ መልካም እንደ ሠሩ አድርገውም በባልንጀሮቻቸው ይመካሉ።
[14] ዝሙትና ከልካይ የሌለባት ኀጢአትም በዐይኖቻቸው ሞልተዋል፤ አእምሮ የሌላቸውን ሰዎች ነፍሳት ያታልላሉ፤ ሥራቸውም ቅሚያ ነው፤ ለልጆቻቸውም መርገምን ያተርፋሉ።
[15] የእውነት መንገድን ትተው ተሳሳቱ፤ የዐመፅን ዋጋ የወደዳትን የባሶርን ልጅ የበለዓምን መንገድም ተከተሉ።
[16] በለዓምንም የማይናገር አህያ በኀጢአቱ ዘለፈው፤ በሰው አነጋገርም ተናግሮ የነቢዩን እብድነት አገደ።
[17] ለዘለዓለም የጨለማ ፍርድ የተጠበቁ እነዚህ የደረቀች የውኃ ጕuድጓድና ነፋስ የሚበትነው ጉም ናቸው።
[18] ከኀጢአት ታላላቆቹን ይናገራሉና፤ በሥጋ በሚሠሩት የዝሙት ሥራቸውም ወደ በደል ከገቡት ለጥቂት ያመለጡትን ሰዎች ያስታሉ።
[19] የነጻነትን ሕግ ተምረው ራሳቸው ለኀጢአት የሚገዙ ናቸው፤ ሰው ሁሉ ለታዘዘለት ይገዛልና።
[20] ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ፥ ከዚህ ዓለም ኀጢአት ከተለዩ፥ ነገር ግን እንደ ገና ተመልሰው ታስረው ከተገዙለት፥ የኋለኛው በደላቸው ከፊተኛው የሚብስ ይሆንባቸዋልና።
[21] ዐውቀዋት ከተሰጠቻቸው ከከበረች ትእዛዝ ወደ ኋላቸው ከሚመለሱ ይልቅ የጽድቅን መንገድ ባላወቌት በተሻላቸው ነበር።
[22] “ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፤ ዕሪያም ታጥባ ለመንከባለል ወደ ጭቃ ተመለሰች ” እንደሚባል እውነተኟች ምሳሌዎች ሆነውባቸዋል።