[1] ከኢየሱስ ክርስቶስ ባርያና ሐዋርያ ከስምዖን ጴጥሮስ፥ በአምላካችንና በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ ካገኘነው ከእኛ ጋር የተካከለ የክብር እምነትን ላገኙ፥
[2] አምላካችንንና ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።
[3] በመለኮቱ ኀይል ለሕይወትና ለመልካም አምልኮ የምንሻውን ነገር ሁሉ የሰጠን፥ እርሱንም በማወቅ በክብሩና በበጎነቱ የጠራን እርሱ ነው።
[4] በእርሱም ፥ የዚህን ዓለም የጥፋት ምኟት እየሸሻችሁ፥ በዚህ የክብሩ ወራሾች ትሆኑ ዘንድ፥ የከበረውንና ታላቅ የሆነውን ተስፋውን ሰጠን።
[5] እናንተ ግን በሥራዉ ሁሉ እየተጋችሁ፥ በእምነት በጎነትን፥ በበጎነትም ዕውቀትን ጨምሩ፤
[6] በዕውቀትም ንጽሕናን፥ በንጽሕናም ትዕግሥትን፥ በትዕግሥትም እግዚአብሔርን ማምለክን፥
[7] እግዚአብሔርንም በማምለክ ወንድማማችነትን፥ በወንድማማችነትም ፍቅርን ጨምሩ፤
[8] እነዚህ ነገሮች ለእናንተ ሆነው ቢበዙ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ያደርጓችኋልና።
[9] እነዚህ ነገሮች የሌሉት ዕውር ነውና፥ በቅርብ ያለውን ብቻ ያያል፤ የቀደመውንም የኀጢአቱን መንጻት ረስቶአል።
[10] ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፥ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ፥ ከፊት ይልቅ ትጉ፤ እነዚህንም ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉም።
[11] እንዲሁ ወደ ዘለዓለሙ ወደ ጌታችንና መድኀኒታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት መግባት በምልዐት ይሰጣችኋል።
[12] ስለዚህም እነዚህን ነገሮች ምንም ብታውቁ፥ በእናንተም ዘንድ ባለ ዕውነት ምንም ብትጸኑ፥ ስለ እነዚህ ዘወትር አሳስባችሁ ዘንድ ቸል አልልም።
[13] ለእኔስ በዚህ ሥጋዬ ሳለሁ በማሳሰብ አነቃቃችሁ ዘንድ፥ የሚገባኝ ይመስለኛል።
[14] ጌታችን ኢየሱስ ክርቶስ እንደ ነገረኝ፥ ከእናንተ መለየቴ ፈጥኖ እንደሚሆን ዐውቃለሁና።
[15] ደግሞም ይህች ትእዛዝ ዘወትር በእናንተ ዘንድ እንድትኖር፥ ከሞቴም በኋላ እንድታስቡአትና እንደ አዘዝኋችሁ እንድታደርጉ እተጋለሁ።
[16] የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ኀይሉንና መምጣቱን ስናስተምራችሁ የተከተልነው የፍልስፍና ተረት አይደለምና፥ የእርሱን ገናናነት እኛ ራሳችን አይተን ነው እንጂ።
[17] ከገናናው ክብር ፥ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይህ ነው ” የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ገንዘብ አድርጓልና።
[18] ይህንም ቃል እኛ በተቀደሰው ተራራ አብረነው ሳለን ከሰማይ እንደ ወረደለት ሰምተነዋል።
[19] ደግሞም ከዚህ የሚቀድም ይህን የሚያሳውቅ የነቢያት ቃል አለ፤ ይህንም ሥራችሁን እጅግ አሳምራችሁ ከተመለከታችሁት፥ ቀኒቱ እስክታበራላችሁና በልባችሁ ውስጥ የአጥቢያ ኮከብ እስኪወጣላችሁ ድረስ በጨለማ ስፍራ ውስጥ እንደምታበራ መብራት ይሆንላችኋል።
[20] ይህን በመጀመሪያ ዕወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጕuም አልተፈቀደም።
[21] ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፤ ዳሩ ግን ቅዱሳን ሰዎች ከእግዚአብሔር ተልከው በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው ተናገሩ።