Skip to content
Opens in a new window

[1] አንተ ግን ሕይወት ለሚገኝበት ትምህርት የሚገባውን ተናገር።

[2] ሽማግሌዎች ልከኞች፥ ጭምቶች፥ ራሳቸውን የሚገዙ፥ በእምነትና በፍቅር በመጽናትም ጤናሞች እንዲሆኑ ምከራቸው፤

[3] እንዲሁም አሮጊቶች ሴቶች አካሄዳቸው ለቅዱስ አገልግሎት የሚገባ፥ የማያሙ፥ ለብዙ ወይን ጠጅ የማይገዙ፥ በጎ የሆነውን ነገር የሚያስተምሩ ይሁኑ፤

[4] -

[5] ቆነጃጅትም የእግዚአብሔር ቃል እንዳይሰደብ፥ ባሎቻቸውን የሚወዱ፥ ልጆቻቸውን የሚወዱ፥ ራሳቸውን የሚገዙ፥ ንጹሖች፥ በቤት የሚሠሩ፥ በጎዎች፥ ለባሎቻቸው የሚታዘዙ እንዲሆኑ ይምከሩአቸው።

[6] ጎበዞችም እንዲሁ ራሳቸውን እንዲገዙ ምከራቸው።

[7] -

[8] የሚቃወም ሰው ስለ እኛ የሚናገረውን መጥፎ ነገር ሲያጣ እንዲያፍር፥ በነገር ሁሉ መልካምን በማድረግህ ምሳሌ የሚሆን ራስህን አሳይ፤ በትምህርትህም ደኅንነትን፥ ጭምትነትን፥ ጤናማና የማይነቀፍ ንግግርን ግለጥ።

[9] -

[10] ባሪያዎች ስለ መድኃኒታችን ስለ እግዚአብሔር የሚሆነውን ትምህርት በሁሉ ነገር ያስመሰግኑ ዘንድ፥ ለገዛ ጌቶቻቸው እንዲገዙ በሁሉም ደስ እንዲያሰኙ፥ ሳይቃወሙና ሳይሰርቁም በጎ ታማኝነትን ሁሉ እንዲያሳዩ ምከራቸው።

[11] ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤

[12] -

[13] ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤

[14] መድኃኒታችንም ከዓመፅ ሁሉ እንዲቤዠን፥ መልካሙንም ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ፥ ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል።

[15] ይህን በሙሉ ሥልጣን ተናገርና ምከር ገሥጽም፤ ማንም አይናቅህ።

ወደ ቲቶ። — Chapters