[1] ወንድሞች ሆይ፥ የልቤ በጎ ፈቃድና ስለ እስራኤል ወደ እግዚአብሔር ልመናዬ እንዲድኑ ነው።
[2] በእውቀት አይቅኑ እንጂ ለእግዚአብሔር እንዲቀኑ እመሰክርላቸዋለሁና።
[3] የእግዚአብሔርን ጽድቅ ሳያውቁ የራሳቸውንም ጽድቅ ሊያቆሙ ሲፈልጉ፥ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም።
[4] የሚያምኑ ሁሉ ይጸድቁ ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና።
[5] ሙሴ ከሕግ የሆነውን ጽድቅ የሚያደርገው ሰው በእርሱ በሕይወት እንዲኖር ጽፎአልና።
[6] ከእምነት የሆነ ጽድቅ ግን እንዲህ ይላል። በልብህ። ማን ወደ ሰማይ ይወጣል? አትበል፤ ይህ ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤
[7] ወይም። በልብህ። ወደ ጥልቁ ማን ይወርዳል? አትበል፤ ይህ ክርስቶስን ከሙታን ለማውጣት ነው።
[8] ነገር ግን ምን ይላል? በአፍህ በልብህም ሆኖ ቃሉ ቀርቦልሃል፤ ይህም የምንሰብከው የእምነት ቃል ነው።
[9] ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤
[10] ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና።
[11] መጽሐፍ። በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም ይላልና።
[12] በአይሁዳዊና በግሪክ ሰው መካከል ልዩነት የለምና፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፥ ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው፤
[13] የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና።
[14] እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ?
[15] መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው ተብሎ እንደ ተጻፈ ካልተላኩ እንዴት ይሰብካሉ?
[16] ነገር ግን ሁሉ ለምሥራቹ ቃል አልታዘዙም። ኢሳይያስ። ጌታ ሆይ፥ ምስክርነታችንን ማን አመነ? ብሎአልና።
[17] እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው።
[18] ዳሩ ግን። ባይሰሙ ነው ወይ? እላለሁ። በእውነት። ድምፃቸው በምድር ሁሉ ላይ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ።
[19] ነገር ግን። እስራኤል ባያውቁ ነው ወይ? እላለሁ። ሙሴ አስቀድሞ። እኔ ሕዝብ በማይሆነው አስቀናችኋለሁ በማያስተውልም ሕዝብ አስቆጣችኋለሁ
[20] ብሎአል። ኢሳይያስም ደፍሮ። ላልፈለጉኝ ተገኘሁ፥ ላልጠየቁኝም ተገለጥሁ አለ።
[21] ስለ እስራኤል ግን። ቀኑን ሁሉ ወደማይታዘዝና ወደሚቃወም ሕዝብ እጆቼን ዘረጋሁ ይላል።