Skip to content
Opens in a new window

[1] ወደ ኢየሩሳሌምም ከደብረ ዘይት አጠገብ ወዳሉቱ ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረቡ ጊዜ፥ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ልኮ።

[2] በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ ወዲያውም ወደ እርስዋ ገብታችሁ ከሰው ማንም ገና ያልተቀመጠበት ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ።

[3] ማንም። ስለ ምን እንዲህ ታደርጋላችሁ? ቢላችሁ። ለጌታ ያስፈልገዋል በሉት፥ ወዲያውም ደግሞ ወደዚህ ይሰደዋል አላቸው።

[4] ሄዱም ውርንጫውንም በመንገድ መተላለፊያ በደጅ ውጭ ታስሮ አገኙት፥ ፈቱትም።

[5] በዚያም ከቆሙት አንዳንዶቹ። ውርንጫውን የምትፈቱት ምን ልታደርጉት ነው አሉአቸው።

[6] እነርሱም ኢየሱስ እንዳዘዘ አሉአቸው፤ ተዉአቸውም።

[7] ውርንጫውንም ወደ ኢየሱስ አመጡት፥ ልብሳቸውንም በላዩ ጣሉ፥ ተቀመጠበትም።

[8] ብዙ ሰዎችም ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፥ ሌሎችም ከዛፍ ቅጠሎችን እየቈረጡ ያነጥፉ ነበር።

[9] የሚቀድሙትም የሚከተሉትም። ሆሣዕና፤ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤

[10] በጌታ ስም የምትመጣ የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከች ናት፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር።

[11] ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ መቅደስ ገባ፤ ዘወር ብሎም ሁሉን ከተመለከተ በኋላ፥ ጊዜው መሽቶ ስለ ነበረ ከአሥራ ሁለቱ ጋር ወደ ቢታንያ ወጣ።

[12] በማግሥቱም ከቢታንያ ሲወጡ ተራበ።

[13] ቅጠልም ያላት በለስ ከሩቅ አይቶ ምናልባት አንዳች ይገኝባት እንደ ሆነ ብሎ መጣ፥ ነገር ግን የበለስ ወራት አልነበረምና መጥቶ ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም።

[14] መልሶም። ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ አላት። ደቀ መዛሙርቱም ሰሙ።

[15] ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ። ወደ መቅደስም ገብቶ በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ያወጣ ጀመር፥ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጭዎችንም ወንበሮች ገለበጠ፤

[16] ዕቃም ተሸክሞ ማንም በመቅደስ ሊያልፍ አልፈቀደም።

[17] አስተማራቸውም። ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ የተጻፈ አይደለምን? እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት አላቸው።

[18] የካህናት አለቆችም ጻፎችም ሰምተው፥ ሕዝቡ ሁሉ በትምህርቱ ይገረሙ ስለ ነበር ይፈሩት ነበርና እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ፈለጉ።

[19] ማታ ማታም ከከተማ ወደ ውጭ ይወጣ ነበር።

[20] ማለዳም ሲያልፉ በለሲቱን ከሥርዋ ደርቃ አዩአት።

[21] ጴጥሮስም ትዝ ብሎት። መምህር ሆይ፥ እነሆ፥ የረገምሃት በለስ ደርቃለች አለው።

[22] ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። በእግዚአብሔር እመኑ።

[23] እውነት እላችኋለሁ፥ ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን በልቡ ሳይጠራጠር፥ ይህን ተራራ። ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ቢል ይሆንለታል።

[24] ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል።

[25] ለጸሎትም በቆማችሁ ጊዜ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁ ደግሞ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ፥ በማንም ላይ አንዳች ቢኖርባችሁ ይቅር በሉት።

[26] እናንተ ግን ይቅር ባትሉ በሰማያት ያለው አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም።

[27] ደግሞም ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። እርሱም በመቅደስ ሲመላለስ፥ የካህናት አለቆችና ጻፎች ሽማግሌዎችም ወደ እርሱ መጥተው።

[28] እነዚህን በምን ሥልጣን ታደርጋለህ? ወይስ እነዚህን ለማድረግ ይህን ሥልጣን ማን ሰጠህ? አሉት።

[29] ኢየሱስም። እኔም አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፥ እናንተም መልሱልኝ፥ እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ።

[30] የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበረችን ወይስ ከሰው? መልሱልኝ አላቸው።

[31] እርስ በርሳቸውም ሲነጋገሩ። ከሰማይ ነው ብንል። እንግዲያውስ ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤

[32] ነገር ግን። ከሰው ነው እንበልን? አሉ፤ ሁሉ ዮሐንስን በእውነት እንደ ነቢይ ያዩት ነበርና ሕዝቡን ፈሩ።

[33] ለኢየሱስም መልሰው። አናውቅም አሉት ኢየሱስም። እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም አላቸው።

የማርቆስ ወንጌል። — Chapters