[1] የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?
[2] ይህን ብቻ ከእናንተ እንድማር እወዳለሁ፤ በሕግ ሥራ ወይም ከእምነት ጋር በሆነ መስማት መንፈስን ተቀበላችሁን?
[3] እንዲህን የማታስተውሉ ናችሁ? በመንፈስ ጀምራችሁ አሁን በሥጋ ትፈጽማላችሁን?
[4] በውኑ ከንቱ እንደ ሆነስ እንደዚህ ያለ መከራ በከንቱ ተቀበላችሁን?
[5] እንግዲህ መንፈስን የሚሰጣችሁ በእናንተም ዘንድ ተአምራት የሚያደርግ፥ በሕግ ሥራ ነውን ወይስ ከእምነት ጋር በሆነ መስማት ነው?
[6] እንዲሁ አብርሃም በእግዚአብሔር አመነና ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት።
[7] እንኪያስ ከእምነት የሆኑት እነዚህ የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ እወቁ።
[8] መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ። በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ።
[9] እንደዚህ ከእምነት የሆኑት ካመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ።
[10] ከሕግ ሥራ የሆኑት ሁሉ በእርግማን በታች ናቸውና፤ በሕግ መጽሐፍ በተጻፉት ሁሉ ጸንቶ የማይኖር የማያደርግም ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና።
[11] ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎአልና ማንም በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንዳይጸድቅ ግልጥ ነው።
[12] ሕግም ከእምነት አይደለም ነገር ግን። የሚያደርገው ይኖርበታል ተብሎአል።
[13] በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን፤
[14] የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል፥ የአብርሃም በረከት ወደ አሕዛብ በኢየሱስ ክርስቶስ ይደርስላቸው ዘንድ።
[15] ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ሰው ልማድ እላለሁ። የሰው ስንኳ ቢሆን እርግጠኛውን ኪዳን ማንም አይንቅም ወይም አይጨምርበትም።
[16] ለአብርሃምና ለዘሩም የተስፋው ቃል ተነገረ። ስለ ብዙዎች እንደሚነገር። ለዘሮቹም አይልም፤ ስለ አንድ እንደሚነገር ግን። ለዘርህም ይላል፥ እርሱም ክርስቶስ።
[17] ይህንም እላለሁ፤ ከአራት መቶ ሠላሳ ዓመት በኋላ የተሰጠው ሕግ አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተረጋገጠውን ኪዳን የተስፋውን ቃል እስኪሽር ድረስ አያፈርስም።
[18] ርስቱ በሕግ ቢሆንስ እንግዲያስ በተስፋ ቃል አይሆንም፤ በተስፋ ቃል ግን እግዚአብሔር ለአብርሃም ሰጥቶአል።
[19] እንግዲህ ሕግ ምንድር ነው? ተስፋው የተሰጠው ዘር እስኪመጣ ድረስ በመካከለኛ እጅ በመላእክት በኩል ስለ ሕግ መተላለፍ ተጨመረ።
[20] መካከለኛውም ለአንድ ብቻ አይደለም እግዚአብሔር ግን አንድ ነው።
[21] እንግዲህ ሕግ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል የሚቃወም ነውን? አይደለም። ሕያው ሊያደርግ የሚቻለው ሕግ ተሰጥቶ ቢሆንስ በእውነት ጽድቅ ከሕግ በሆነ ነበር፤
[22] ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ከማመን የሆነው የተስፋ ቃል ለሚያምኑ ይሰጥ ዘንድ መጽሐፍ ከኃጢአት በታች ሁሉን ዘግቶታል።
[23] እምነትም ሳይመጣ ሊገለጥ ላለው እምነት ተዘግተን ከሕግ በታች እንጠበቅ ነበር።
[24] እንደዚህ በእምነት እንጸድቅ ዘንድ ሕግ ወደ ክርስቶስ የሚያመጣ ሞግዚታችን ሆኖአል፤
[25] እምነት ግን መጥቶአልና ከእንግዲህ ወዲህ ከሞግዚት በታች አይደለንም።
[26] በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤
[27] ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና።
[28] አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና።
[29] እናንተም የክርስቶስ ከሆናችሁ እንኪያስ የአብርሃም ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ።