[1] እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ።
[2] በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም።
[3] ሞታችኋልና፥ ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና።
[4] ሕይወታችሁ የሆነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ።
[5] እንግዲህ በምድር ያሉቱን ብልቶቻችሁን ግደሉ፥ እነዚህም ዝሙትና ርኵሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም ጣኦትንም ማምለክ የሆነ መጎምጀት ነው።
[6] በእነዚህም ጠንቅ የእግዚአብሔር ቍጣ በማይታዘዙ ልጆች ላይ ይመጣል።
[7] እናንተም ደግሞ ትኖሩባቸው በነበራችሁ ጊዜ፥ በፊት በእነዚህ ተመላለሳችሁ።
[8] አሁን ግን እናንተ ደግሞ ቍጣንና ንዴትን ክፋትንም፥ ከአፋችሁም ስድብን የሚያሳፍርንም ንግግር እነዚህን ሁሉ አስወግዱ።
[9] እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ፥ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፋችሁታልና፥
[10] የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል።
[11] በዚያም የግሪክ ሰው አይሁዳዊም የተገረዘም ያልተገረዘም አረማዊም እስኩቴስም ባሪያም ጨዋ ሰውም መሆን አልተቻለም፥ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፥ በሁሉም ነው።
[12] እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፥ ምሕረትን፥ ርኅራኄን፥ ቸርነትን፥ ትህትናን፥ የዋህነትን፥ ትዕግሥትን ልበሱ።
[13] እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፥ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፥ ይቅር ተባባሉ። ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ።
[14] በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት።
[15] በአንድ አካልም የተጠራችሁለት ደግሞ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ። የምታመሰግኑም ሁኑ።
[16] የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ። በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ አስተምሩና ገሥጹ። በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ በጸጋው በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ።
[17] እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ፥ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት።
[18] ሚስቶች ሆይ፥ በጌታ እንደሚገባ ለባሎቻችሁ ተገዙ።
[19] ባሎች ሆይ፥ ሚስቶቻችሁን ውደዱ መራራም አትሁኑባቸው።
[20] ልጆች ሆይ፥ ይህ ለጌታ ደስ የሚያሰኝ ነውና በሁሉ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ።
[21] አባቶች ሆይ፥ ልባቸው እንዳይዝል ልጆቻችሁን አታበሳጩአቸው።
[22] ባሪያዎች ሆይ፥ በቅን ልብ ጌታን እየፈራችሁ እንጂ፥ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ ሳትሆኑ፥ በሥጋ ጌቶቻችሁ ለሆኑ በሁሉ ታዘዙ።
[23] ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ፥ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት አድርጉት፥
[24] ከጌታ የርስትን ብድራት እንድትቀበሉ ታውቃላችሁና። የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስ ነውና።
[25] የሚበድልም የበደለውን በብድራት ይቀበላል፥ ለሰው ፊትም አድልዎ የለም።