Skip to content
Opens in a new window

[1] ሽማግሌው በእውነት እኔ ለምወደው ለተወደደው ለጋይዮስ።

[2] ወዳጅ ሆይ፥ ነፍስህ እንደሚከናወን፥ በነገር ሁሉ እንዲከናወንልህና ጤና እንዲኖርህ እጸልያለሁ።

[3] ወንድሞች መጥተው አንተ በእውነት እንደምትሄድ ስለ እውነትህ ሲመሰክሩ እጅግ ደስ ብሎኛልና።

[4] ልጆቼ በእውነት እንዲሄዱ ከመስማት ይልቅ የሚበልጥ ደስታ የለኝም።

[5] ወዳጅ ሆይ፥ ምንም እንግዶች ቢሆኑ፥ ለወንድሞች በምታደርገው ሁሉ የታመነ ሥራ ትሠራለህ፥ እነርሱም በማኅበር ፊት ስለ ፍቅርህ መስክረዋል፤

[6] ለእግዚአብሔር እንደሚገባ አድርገህ በጉዞአቸው ብትረዳ መልካም ታደርጋለህ፤

[7] ከአሕዛብ አንዳች ሳይቀበሉ ስለ ስሙ ወጥተዋልና።

[8] እንግዲህ ከእውነት ጋር አብረን እንድንሠራ እኛ እንዲህ ያሉትን በእንግድነት ልንቀበል ይገባናል።

[9] ወደ ቤተ ክርስቲያን ጻፍሁ፤ ዳሩ ግን ዋናቸው ሊሆን የሚወድ ዲዮጥራጢስ አይቀበለንም።

[10] ስለዚህ፥ እኔ ብመጣ፥ በእኛ ላይ በክፉ ቃል እየለፈለፈ የሚያደርገውን ሥራውን አሳስባለሁ፤ ይህም ሳይበቃው እርሱ ራሱ ወንድሞችን አይቀበልም፥ ሊቀበሉአቸውም የሚወዱትን ከልክሎ ከቤተ ክርስቲያን ያወጣቸዋል።

[11] ወዳጅ ሆይ፥ በጎ የሆነውን እንጂ ክፉን አትምሰል። በጎ የሚያደርግ ከእግዚአብሔር ነው፤ ክፉን የሚያደርግ ግን እግዚአብሔርን አላየውም።

[12] ለድሜጥሮስ ሁሉ ይመሰክሩለታል፥ እውነት ራስዋም ትመሰክርለታለች፤ እኛም ደግሞ እንመሰክርለታለን፥ ምስክርነታችንም እውነት እንደ ሆነ ታውቃላችሁ።

[13] ልጽፍልህ የምፈልገው ብዙ ነገር ነበረኝ፥ ዳሩ ግን በቀለምና በብርዕ ልጽፍልህ አልወድም፤

[14] ነገር ግን ወዲያው ላይህ ተስፋ አደርጋለሁ፥ አፍ ለአፍም እንነጋገራለን።

[15] ሰላም ለአንተ ይሁን። ወዳጆች ሰላምታ ያቀርቡልሃል። ወዳጆችን በየስማቸው እየጠራህ ሰላምታ አቅርብልኝ።