Skip to content
Opens in a new window

[1] እንግዲህ ክፋትን ሁሉ ተንኰልንም ሁሉ ግብዝነትንም ቅንዓትንም ሐሜትንም ሁሉ አስወግዳችሁ፥

[2] -

[3] ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደ ሆነ፥ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ።

[4] በሰውም ወደ ተጣለ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ወደ ተመረጠና ክቡር ወደ ሆነው ወደ ሕያው ድንጋይ ወደ እርሱ እየቀረባችሁ፥

[5] እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ።

[6] በመጽሐፍ። እነሆ፥ የተመረጠና የከበረን የማዕዘን ራስ ድንጋይ በጽዮን አኖራለሁ በእርሱም የሚያምን አያፍርም ተብሎ ተጽፎአልና።

[7] እንግዲህ ክብሩ ለእናንተ ለምታምኑት ነው፤ ለማያምኑ ግን አናጢዎች የጣሉት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ የዕንቅፋትም ድንጋይ የማሰናከያም ዓለት ሆነ፤

[8] የማያምኑ ስለ ሆኑ በቃሉ ይሰናከሉበታልና፤ ለዚህ ደግሞ የተመደቡ ናቸው።

[9] እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤

[10] እናንተ ቀድሞ ወገን አልነበራችሁም አሁን ግን የእግዚአብሔር ወገን ናችሁ፤ እናንተ ምሕረት ያገኛችሁ አልነበራችሁም አሁን ግን ምሕረትን አግኝታችኋል።

[11] ወዳጆች ሆይ፥ ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት ትርቁ ዘንድ እንግዶችና መጻተኞች እንደ መሆናችሁ እለምናችኋለሁ፤

[12] ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ፥ ክፉ እንደምታደርጉ በዚያ እናንተን በሚያሙበት ነገር፥ በሚጎበኝበት ቀን እግዚአብሔርን ያከብሩት ዘንድ በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን።

[13] ስለ ጌታ ብላችሁ ለሰው ሥርዓት ሁሉ ተገዙ፤ ለንጉሥም ቢሆን፥ ከሁሉ በላይ ነውና፤

[14] ለመኳንንትም ቢሆን፥ ክፉ የሚያደርጉትን ለመቅጣት በጎም የሚያደርጉትን ለማመስገን ከእርሱ ተልከዋልና ተገዙ።

[15] በጎ እያደረጋችሁ፥ የማያውቁትን ሞኞች ዝም ታሰኙ ዘንድ እንዲህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነውና፤

[16] አርነት ወጥታችሁ እንደ እግዚአብሔር ባሪያዎች ሁኑ እንጂ ያ አርነት ለክፋት መሸፈኛ እንዲሆን አታድርጉ።

[17] ሁሉን አክብሩ፥ ወንድሞችን ውደዱ፥ እግዚአብሔርን ፍሩ፥ ንጉሥን አክብሩ።

[18] ሎሌዎች ሆይ፥ ለበጎዎችና ለገሮች ጌቶቻችሁ ብቻ ሳይሆን ለጠማሞች ደግሞ በፍርሃት ሁሉ ተገዙ።

[19] በግፍ መከራን የሚቀበል ሰው እግዚአብሔርን እያሰበ ኃዘንን ቢታገሥ ምስጋና ይገባዋልና።

[20] ኃጢአት አድርጋችሁ ስትጎሰሙ ብትታገሡ፥ ምን ክብር አለበት? ነገር ግን መልካም አድርጋችሁ መከራን ስትቀበሉ ብትታገሡ፥ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ይገባዋል።

[21] የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና።

[22] እርሱም ኃጢአት አላደረገም፥ ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም፤

[23] ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤

[24] ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፤

[25] በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ። እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበርና፥ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል።

የጴጥሮስ መልእክት። — Chapters