[1] ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
[2] እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።
[3] ትእዛዛቱንም ብንጠብቅ በዚህ እንዳወቅነው እናውቃለን።
[4] አውቄዋለሁ የሚል ትእዛዛቱንም የማይጠብቅ ውሸተኛ ነው እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም።
[5] ቃሉን ግን የሚጠብቅ ሁሉ በእርሱ የእግዚአብሔር ፍቅር በእውነት ተፈጽሞአል። በእርሱ እንዳለን በዚህ እናውቃለን፤
[6] በእርሱ እኖራለሁ የሚል እርሱ እንደ ተመላለሰ ራሱ ደግሞ ሊመላለስ ይገባዋል።
[7] ወንድሞች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረቻችሁ አሮጌ ትእዛዝ እንጂ የምጽፍላችሁ አዲስ ትእዛዝ አይደለችም፤ አሮጌይቱ ትእዛዝ የሰማችኋት ቃል ናት።
[8] ዳግመኛ አዲስ ትእዛዝን እጽፍላችኋለሁ፥ ይህም ነገር በእርሱ በእናንተም እውነተኛ ነው፤ ጨለማው ያልፋልና እውነተኛውም ብርሃን አሁን ይበራል።
[9] በብርሃን አለሁ የሚል ወንድሙንም የሚጠላ እስከ አሁን በጨለማ አለ።
[10] ወንድሙንም የሚወድ በብርሃን ይኖራል ማሰናከያም የለበትም፤
[11] ወንድሙን የሚጠላ ግን በጨለማ አለ፥ በጨለማም ይመላለሳል፥ የሚሄድበትንም አያውቅም፥ ጨለማው ዓይኖቹን አሳውሮታልና።
[12] ልጆች ሆይ፥ ኃጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና እጽፍላችኋለሁ።
[13] አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ጎበዞች ሆይ፥ ክፉውን አሸንፋችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ልጆች ሆይ፥ አብን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ።
[14] አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ጐበዞች ሆይ፥ ብርቱዎች ስለ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም ቃል በእናንተ ስለሚኖር ክፉውንም ስለ አሸነፋችሁ እጽፍላችኋለሁ።
[15] -
[16] ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።
[17] ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።
[18] ልጆች ሆይ፥ መጨረሻው ሰዓት ነው፥ የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደ ሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል፤ ስለዚህም መጨረሻው ሰዓት እንደ ሆነ እናውቃለን።
[19] ከእኛ ዘንድ ወጡ፥ ዳሩ ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገንስ ቢሆኑ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር፤ ነገር ግን ሁሉ ከእኛ ወገን እንዳልሆኑ ይገለጡ ዘንድ ወጡ።
[20] እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ።
[21] እውነትን የምታውቁ ስለ ሆናችሁ፥ ውሸትም ሁሉ ከእውነት እንዳልሆነ ስለምታውቁ እንጂ እውነትን ስለማታውቁ አልጽፍላችሁም።
[22] ክርስቶስ አይደለም ብሎ ኢየሱስን ከሚክድ በቀር ውሸተኛው ማን ነው? አብንና ወልድን የሚክድ ይህ የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው።
[23] ወልድን የሚክድ ሁሉ አብ እንኳ የለውም፤ በወልድ የሚታመን አብ ደግሞ አለው።
[24] እናንተስ ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ጸንቶ ይኑር። ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ቢኖር፥ እናንተ ደግሞ በወልድና በአብ ትኖራላችሁ።
[25] እርሱም የሰጠን ተስፋ ይህ የዘላለም ሕይወት ነው።
[26] ስለሚያስቱአችሁ ሰዎች ይህን ጽፌላችኋለሁ።
[27] እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ።
[28] አሁንም፥ ልጆች ሆይ፥ በሚገለጥበት ጊዜ እምነት እንዲሆንልን በመምጣቱም በእርሱ ፊት እንዳናፍር በእርሱ ኑሩ።
[29] ጻድቅ እንደ ሆነ ካወቃችሁ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ከእርሱ እንደ ተወለደ እወቁ።